Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የወጣቶች ኮከስ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የሴት ወጣቶች ኮከስ ይፋ ተደረገ፡፡
በመድረኩ፥ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ በአፍሪካ ህብረት የሴቶች፣ የሰላምና ጸጥታ ልዩ መልእክተኛ ቤኒታ ዲዮፕ፣ በኢትዮጵያ የአይርላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብሬነን እንዲሁም የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት የወጣቶች ኮከስ ሰብሳቢ ዶክተር ጆሃኒ ቤዋ ተገኝተዋል፡፡
ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር÷ በሰላምና ደህንነት አጀንዳ ላይ ወጣት ሴቶችን ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ሚናቸውን ማጎልበት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በይፋ የተመሰረተው የሴት ወጣቶች ኮከስ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የተመረጡትን ወጣቶች በአፍሪካ ደረጃ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት፡፡
በዋናነት ሴት አመራሮችን በአህጉሪቱ ልማት፣ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በሰብአዊ ድጋፍ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ማሳደግ የኮከሱ ዓላማ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረትና የወጣቶች ኮከስ በተለያዩ አገራት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን÷ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ሴት አመራሮች ጥምረት በፈረንጆቹ በ2019 ይፋ ሆኖ በስራ ላይ የቆየ ነው፡፡
ባዛሬው መድረክም የኢትዮጵያ ሴት ወጣቶች የሚወከሉበት ኮከስ በይፋ መመስረቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ሴት ወጣቶች ኮከስ በመወከል ወጣት እድላዊት ደረጄ÷ በአፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወጣቶችን በሰላምና ደህንነት ውይይቶች ላይ የማሳተፍን አስፈላጊነት አብራርታለች፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.