Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች በቀጠናዊ ትብብርና የአካባቢውን የልማት ስራዎች ላይ ውይይት አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች በቀጠናዊ ትብብርና በአካባቢው የልማት ስራዎች ላይ ውይይት ማካሄዳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው የገንዘብ ሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ በዋነኛነት የአካባቢውን ልማት ለማጎልበትና በቀጠናው እየተስተዋሉ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ያተኮረ  ውይይት ነው ያካሄዱት፡፡

ቀጠናውን በአሁኑ ወቅት እየፈተኑ የሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን የምጣኔ ሀብት ቀውስና የበረሃ አንበጣ በግብርና እና በምግብ ዋስትና ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፋት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የኮሮና ወረርሽኝ በተለይም ዝቅተኛ ምጣኔ ሀብት ባላቸው የአፍሪካ ሀገራት ላይ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራትም በወረርሽኙ ጉዳት የተነሳ ያለባቸውን የውጭ ዕዳ ወቅቱን ጠብቀው መክፈል አለመቻላቸው እና ሁኔታውም ከዚህ የበለጠ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይከሰት ሀገራቱ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ሀገራት ከወረርሽኙ ተፅዕኖ ማገገም እንዲችሉም ደህንነቱ የተጠበቀ ውጤታማና በስፋት ሊገኝ የሚችል የኮቪድ19 ክትባት በፍጥነት ማግኘትና ማሰማራጨት ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የቀጠናውን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሴክሬታሪያት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን  የተገኙ ውጤቶች እንዳይሸረሸሩ እየገጠሙን ያሉ ተግዳሮቶች እና ድንበር ተሻጋሪ ችግሮችን በብቃት ለመፍታት እስከአሁን ያሉ የትብብር ስልቶችን እንደገና ለማጤን እና አጋርነታችንን ለማጠንከር ይበልጥ መስራት እንደሚገባም አውስተዋል፡፡

በፅህፈት ቤቱ አስተባባሪነት እስከአሁን ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል በተምሳሌትነት በንግድ ውህደት ላይ  የቀረበውን የፖሊሲ እርምጃዎች  አንስተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጅቡቲ፣ የኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራና ሱዳን የገንዘብና የልማት ሚኒስትሮች መሳተፋቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.