Fana: At a Speed of Life!

የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የስራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የዘጠኝ ወራት የተቋማት የስራ አፈጻጸም ግምገማ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ መድረኩ በአይነቱ ልዩና የመጀመሪያው መሆኑን ገልፀው ከአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለተግባሩ ስኬት የ10 አመት ስትራቴጅክ እቅድ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ መድረኩ የ10 አመቱን የልማት መሪ እቅድ ይፋ ማድረግ፣ የዘጠኝ ወራት የተቋማት ስራ አፈፃጸም መገምገምና የቀጣይ ስድስት ወር እቅድ ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጥን ዓላማው ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያ ጌታ በበኩላቸው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የሃገሪቱን የእድገት ጉዞ ለማፋጠን ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስታውሰው ለዘርፉ ስኬታማነት ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ውይይቱ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን የአክሱም ፣ አምቦ፣ አርሲ፣ አሶሳ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ ፣ ዲላ ፣ድሬዳዋ ፣ ጅግጅጋ ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ፣ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤ ፣ ወለጋ እንዲሁም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንቶችና የካውንስል አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአስጨናቂ ጉዱ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.