Fana: At a Speed of Life!

የኢራኑ ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ በአሜሪካ ወታደሮች ተገደሉ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒን መግደሏን አስታወቀች።

ጀኔራል ቃሲም ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውን የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

በወቅቱ በባግዳድ አውሮፕላን ማረፊያ በተሽከርካሪ እየንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት በአነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውም ነው የተነገረው።

በተፈጸመው ጥቃት ከእርሳቸው በተጨማሪ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች አብረው ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነግሯል።

ፔንታገን ጥቃቱ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ የተፈጸመ ስለመሆኑም ገልጿል።

መስሪያ ቤቱ እርምጃው በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የአሜሪካ መከላከያ አባላትን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ተወስዷልም ነው ያለው።

አሜሪካ ጥቅሟን ለማስከበርና በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ዜጎቿን ደህንነት ለመጠበቅ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ትወስዳለችም ነው ያለው በመግለጫው።

በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከአንድ ቀን በፊት ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።

አሜሪካም በወቅቱ የተፈጸመው ጥቃት በጄኔራሉ አቀናባሪነት የተፈጸመ ነው ስትል ኮንናለች።

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከባድ አፀፋዊ ምላሽ ይጠብቃቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የእርሳቸውን ህልፈት ተከትሎም የሶስት ቀን ብሄራዊ ሃዘን አውጀዋል።

ከጀኔራሉ የህልፈት ዜና በኋላ የነዳጅ ዋጋ በ4 በመቶ ማሻቀቡ ተነግሯል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.