Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል ፈተናዎችን በጽናት ተቋቁሞ ወደ ብሩህ ጊዜ በተስፋ የመሻገር በዓል ነው-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣መስከረም 21፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከኦሮሞ ሕዝብ ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ፤ ይህን ትልቅ ባህላዊ ዕሴት ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱ ቀደምት አባቶቻችን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ኢሬቻ መጪዉ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ቃል የምንገባበት በዓል በመሆኑ ሁሉን አስተካክሎና ዉብ አድርጎ የፈጠረ ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣ ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞት የሚቀርብበት በዓል ነዉ ብለዋል፡፡
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ሙሉ ቃልም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ

የኦሮሞ ሕዝብ ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና ዕርቅን በሚገነቡ ባህላዊ ዕሴቶች እጅጉን የበለጸገ ሕዝብ ነዉ፡፡

ከእነዚህ ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነዉ፡፡

ይህን ትልቅ ባህላዊ ዕሴት ከትዉልድወደ ትዉልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱ ቀደምት አባቶቻችን ክብርና ምስጋናይገባቸዋል፡፡

ኢሬቻ – የምስጋና፣ የዕርቅ እና የሰላም በዓል ነዉ፡፡ የፍቅር፣ የይቅርታ እና የአንድነት በዓል ነዉ፡፡

ኢሬቻመጪዉ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ቃል የምንገባበት በዓል ነዉ፡፡ ሁሉን አስተካክሎና ዉብ አድርጎ የፈጠረ ፈጣሪየሚመሰገንበት፣ ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞት የሚቀርብበት በዓል ነዉ፡፡

ኢሬቻ- ትናንትን የማመስገኛ እና ነገን ሰላም የማድረጊያ በዓል ነው፡፡

ያለፈውን ዓመት አሳልፎ ለዚህያደረሰንን ፈጣሪ የማመስገኛ እና ቀጣዩን ዓመት በመልካም ምኞትና በመልካም ተግባር የመጀመሪያ በዓል
ነው፡፡

ሰው በዋናነት የሚኖረው ከተፈጥሮ ጋርና በተፈጥሮ ውስጥ ነው፡፡

የተፈጥሮ ጤና መሆን የሰው ልጅንጤና ይወስነዋል፡፡

የተፈጥሮ መበላሸትም የሰው ልጅን ሥጋት ይጨምረዋል፡፡ ለዚህ ነው ቀደምቶቻችንለተፈጥሮ ዋጋ የሚሰጠውን የኢሬቻን በዓል እንድናከብረው የሠሩልን፡፡

የክረምቱ ወቅት የምግብ እጥረት እና የመገናኛ ችግር የሚከሠትበት ወቅት ነው፡፡

ወባን የመሳሰሉ ወረርሽኞችየሚያይሉበት ጊዜ ነው፡፡

በዚህ የተነሣ የችግር ወቅት ተደርጎ፣ በጨለማ ተመስሎ ይወሰድ ነበር፡፡

ወንዞችበመሙላታቸው ምክንያት መገናኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከላይ ዝናቡ፣ ከታች ጭቃው ኑሮን ከባድ ያደርገዋል፡፡

በጥር ወር አካባቢ የተሰበሰበው ምርት በክረምት ወቅት ስለሚያልቅ፣ ክረምቱ በቂ ምግብ የሚገኝበት ወቅትአይደለም፡፡

ይህ ወቅት የሚያልፈው ፈታኙን ጊዜ በጠንካራ ትግል በመገዳደር ነው፡፡

በአንድ በኩል ለወቅቱ የሚሆነውንሰብል በማምረት፣ በሌላ በኩል ለዘለቄታው የሚበጀውን እህል በማረስ ነው – መከራው የሚሸነፈው፡፡

በቆሎ፣ ገብስና ድንችን የመሳሰሉ ሰብሎችን ለክረምቱ እንዲደርሱለት አድርጎ ገበሬው ይዘራል፡፡

ሌሎቹንደግሞ ለዓመት ጉርስ እንዲሆኑት ያመርታቸዋል፡፡

ጤናን አጥብቆ በመጠበቅ ነው ወረርሽኙንየሚቋቋመው፡፡

ኢሬቻ- በንጹሕ ኅሊናና አስተሳሰብ በፍጹም ደስታ የሚከበር በዓል ነዉ፡፡

በባህሉ መሠረት ወደ ኢሬቻበዓል ከመገባቱ በፊት የተጣላ ታርቆ፣ ቂም እና ጥላቻ በይቅርታና ፍቅር ታክሞ፣ ለሰዉ ልጆች ሁሉ መልካም
ምኞትን በመግለጽ በታላቅ አንድነትና ኅብረት የሚከበር በዓል ነዉ፡፡

በዓሉ የምስጋናና የአንድነት በዓልበመሆኑ በኦሮሞ ሕዝብ ብቻ የሚከበር አይደለም፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የኢሬቻን መሠረታዊ ዕሴቶች የሚጋሩ በመሆናቸዉ በበዓሉ ላይ በባህላዊ አልባሶቻቸዉ ተዉበዉ፣ እያዜሙ እናእየጨፈሩ የሚያደምቁት፣ ኢሬቻ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስተሣሥር አንዱ ጠንካራ ሐረግ መሆኑን
በተግባር የሚያሳዩበት ዕለት ነዉ፡፡

ስለሆነም በዓሉ የመላዉ ኢትዮጵያውያን በዓል ነዉ፡፡
ኢሬቻ- የመሻገር በዓል ነዉ፡፡

በጨለማ ከሚመሰለዉ ክረምት ወደ ብርሃናማዉ መጸዉ፣ ከጥላቻ ወደ
ፍቅር፣ ከጠላትነት ወደ ወንድማማችነት፣ ከጸብ ወደ ዕርቅ፣ ከቂም በቀል ወደ ይቅርታ ከክፋት ወደመልካምነት ሽግግር የሚደረግበት በዓል ነዉ፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን የዘንድሮውን ኢሬቻ የምታከብረው በፈተና እና በተስፋ መካከል ሆና ነው፡፡

የክረምቱወቅት ምንም ፈታኝ ወቅት ቢሆን፣ በገበሬዎቻችን ትግል ግን የተስፋ መፀነሻ ወቅት ይሆናል፡፡

በመጸውና በበጋ ወቅቶች ምርት የሚትረፈረፈው በክረምቱ ወቅት በተሠራው ሥራ ነው፡፡

የነገዋ ኢትዮጵያ ብልጽግናእንዲትረፈረፍባት ከፈለግን፣ ዛሬ በአስቸጋሪው ጊዜ ችግሩን የሚያስወግድና መጪውን ዘመን ብሩህ
የሚያደርግ ሥራ መሥራት አለብን፡፡

የሞሉት ወንዞች ይጎድላሉ፤ ጭቃውም ይደርቃል፤ ብርዱም ይሞቃል፤የሰማይ መስኮቶች ይዘጋሉ፤ የምድር ቀላያት ይከደናሉ፡፡

ከማዶ ብሩህ ተስፋ አለ፤ ከክረምቱ ባሻገር የተዘራዉ ቡቃያ ፍሬ ያፈራል፣ አበቦች ይፈካሉ፣ ምድር አረንጓዴትለብሳለች፤ ከናፈቁት ዘመድ ጋር መገናኘት፣ ገበያ መዉጣት፣ መነገድ፣ ከአድማስ ባሻገር በተስፋ ይታያሉ።

ፈተናዎቹን በጽናት ተቋቁሞ ወደ ብሩህ ጊዜ በተስፋ የመሻገር በዓል ነዉ።

የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣የዕርቅ፣ የመቻቻል፣ የቤተሰባዊነት ዕሴቶች የሽግግሩን ፈተናዎች የሚያሻግሩና ወደ ብሩህ ጊዜ የሚያደርሱ
ድልድዮች ናቸዉ። የመሻገሪያ ድልድዩን ደራሽ ጎርፍና ድንገተኛ አዉሎ ነፋስ ሊያነቃንቀዉ ይችል ይሆናል፤ግን ከቶዉኑም ሊያፈርሰዉ አይችልም፡፡ ድልድዩ በማይፈርሱ ዕሴቶች የተዋቀረ ነዉና፡፡

ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያ ከፊቷ የሚያስጎመጅ ጊዜ ይጠብቃታል፡፡

እንደ መጸው የሚያጓጓ፤ እንደ በጋውየሚናፍቅ ጊዜ ከፊታችን እየመጣ ነው፡፡

እንደምታውቁት በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ዘመን የነበረው
ክረምትና የዛሬው ክረምት የተለያየ ነው፡፡

የሰው ልጆች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት የክረምቱን መከራ
ቀንሰውታል፤ መንገዶችንና የመገናኛ መሣሪያዎችን ሠርተው ችግሩን ቀርፈውታል፤ የእርሻ መሣሪያዎችን
ፈልስፈው ግብርናን አቅልለውታል፤ የጤና ተቋማትን አሻሽለው የክረምትን ወረርሽኞች እያጠፏቸው
መጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የገጠማትን ፈተና ማለፍ የምትችለው ፈታኙን አምርረን ስንታገለው ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከፈተና ፈጽሞ መለየት አይቻል ይሆናል፡፡

የፈተናውን ዓይነት መቀየር፣ የፈተናውንም መጠንመቀነስ ግን ይቻላል፡፡

ይህ አሁን የገጠመን ጉጅሌ አብሮን እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም፡፡ ሰንኮፉ ከኢትዮጵያችን ላይ ተነቅሎ መወገድ አለበት፡፡ ባህላችንን፣ እምነታችንን፣ ሥልጣኔያችንን፣ አብሮ የመኖር
ዕሴታችንን፣ ፖለቲካዊ ካፒታላችንን፣ ሉዓላዊነታችንን፣ መልካም ሰብእናችንን አጥፍቶ ባዶ እጃችን ሊያስቀረን የመጣው ሀገር አፍራሽ ቡድን ካልተወገደ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ዓመት አይመጣም፡፡

ገበሬዎቻችን የክረምቱን ወቅት ለመሻገር የሚሆን ሥራ ብቻ አይሠሩም፤ መጪውን ጊዜ ለመዋጀትየሚያስችል ተግባር ጭምር እንጂ፡፡

እኛም አሁን የገጠመንን ፈተና ለማሸነፍ የሚሆን ሥራ ብቻ መሥራት
የለብንም፡፡

የነገውን የብልጽግና ጉዟችንን የሚዋጅ ጭምር እንጂ፡፡

የተወረወሩብን ድንጋዮች ድልድይ እንገንባባቸው፤ ትምህርት ቤት እንሥራባቸው፤ የጤና ተቋም እናንጽባቸው፤ መከላከያችንን እናዘምንባቸው፤ግብርናችንን እናሠልጥንባቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጣችንን እናቀልጥፍባቸው፡፡

ኢትዮጵያ መንገዷን እንደ አዲስ ለመቃኘት በምትዘጋጅበት ዋዜማ ነው የዘንድሮው ኢሬቻ እየተከበረያለው፡፡

ዴሞክራሲያችን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን፣ የፍትሕ ሥርዓታችን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊሥሪታችን፣ የውጭ ግንኙነትና የሀገር ውስጥ ጉዳዮቻችን በአዲስ ቅኝት ይቃኛሉ፡፡

የትናንትናው ስሕተት እንዳይደገም፤ የትናንቱ ፈተና ዳግም እንዳይመጣ፤ የትናንት ፈታኞቻችንም ዳግም ዕድል እንዳያገኙ፤ የትናንቱስብራት እንዲጠገን፤ የትናንቱ መዛነፍ እንዲቃና የሚያደርግ አዲስ ቅኝት ያስፈልገናል፡፡

የክራሩ ጅማቶችየራሳችን ናቸው፡፡ መቃኘትም ያለብን ራሳችን ነን፡፡

የኢሬቻ በዓል ሲከበር ያለፈው ጎርፍ አልፎ በአዲስ ውኃ፣ ደረቁ ሣርም ረግፎ በአዲስ ለምለም ሣር ነው፡፡

ያለፈው ይበቃል – የሚል ነው መልእክቱ፡፡ እውነት ነው ያለፈው ይበቃል፡፡ የደረቁ ሣሮችንና የደፈረሱ ጎርፎችን – በቃችሁን – ብለን በአዲስ ለምለም ሣር በዓሉን እናከብረዋለን፡፡

ነባሩ ምድር አዲስ ሣርያበቅላል፡፡ አዲስ የጠራ ምንጭ ኩልል ብሎ ይወርድበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ የደፈረሱ ጎርፎችን
እምቢ ብለዋል፡፡

የደረቁ ሣሮችን እምቢ ብለዋል፡፡ ለምለም ቄጤማ ይዘው ኩልል ያለውን ምንጭ ፍለጋመጥተዋል፡፡

ማንም ወደ ደረቀው ሣርና ወደ ደፈረሰው ጎርፍ ሊመልሰን አይቻለውም፡፡ የደረቀው ሣርእየወጋ፣ የደፈረሰው ጎርፍ እያሠጋ ሊመልሰን ሞክሮ ነበር፡፡ “ሆ” ብለን፣ አንድ ሆነን፣ አምርረን፣ ወጥተናል፡፡

ከወጣ ውረዶቹና ከፈተናዎቹ ባሻገር ተስፋ አለ፤ የተሻለ ዘመን የተሻለ ሀገር እንደሚኖረን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም በጽናት በተስፋ፣ በጋራ፣ በመቻቻል፣ በቤተሰባዊነት መንፈስ መቆምን ኢሬቻ ያስተምረናል።

ፈተናዎቹን በመቻቻል፣ በመረዳዳት፣ በዕርቅ፣ በይቅርታና በሰላም መሻገር የኢሬቻ አስተምህሮት ነዉ፡፡

መልካም የኢሬቻ በዓል ይሁንልን!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 21፣ 2014 ዓ.

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.