Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዳለው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት መጠናከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዳለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ ገለጹ፡፡

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ በኬንያ ፓርላማ የመከላከያ እና የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰማያት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያ እና ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትና ብሄራዊ ፍላጎት ማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በቀጠናዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመስራት ያላትን ቁርጠኛ አቋም አድንቀዋል፡፡

በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ኢትዮጵያዊያን ከኬንያዊያን ጋር ተቀራርበውና በወንድማማችነት መንፈስ እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡

በድንበር አካባቢ የሚገኙ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች በባህል፣ በቋንቋ፣ በንግድ፣ በግብርና እና በቱሪዝም መስክ ግንኙነታቸውን ማጠንከር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ነው ተወካዩ ያብራሩት፡፡

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተክሌ ተሰማ እንደገለጹት፥ በሱዳን ድንበር አካባቢ የሚታየውን አለመግባበት እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ በውይይት እና በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ችግሮችን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመው፥ ወደፊትም ኢትዮጵያ ለሁሉም የሰላም አማራጮች በሯ ክፍት ነው ሲሉ ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ የግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በተሻለ መልኩ ለማጠናከርና ለማሳለጥ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን መዘርጋት ጉልህ ሚና እንዳለው የኮሚቴው አባል አቶ ሆርዶፋ በቀለ የገለፁ ሲሆን፥ በዚህም ረገድ ከሐዋሳ ሞያሌ የተገነባው የፍጥነት መንገድ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኬንያ ልዑካን ቡድን መሪ ዲዶ ራሶ አሊ በበኩላቸው፥ በሁለቱ ሀገራት ፓርላሜንታዊ ግንኙነት የቀጠናውን የሰላም ሁኔታ ከማጠናከር አኳያ እንዲሁም አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ድንበር ዘለል ግጭቶች እና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የግንኙት ስርዓቱንም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ትብብራቸውን አጠናክረው ከመስቀጠል አኳያ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተቀረርባ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነች ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ፓርላሜንታዊ የግንኙነት ስርዓት የቀጠናውን የሰላም ሁኔታ ከማጠናከር አኳያ እንዲሁም አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ድንበር ዘለል ግጭቶች እና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ የግንኙነት ስርዓቱንም ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ገልፀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.