Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የሱዳን እህትማማችነት ለጋራ እድገት ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የሱዳን እህትማማችነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ መልካም ፍላጎቷ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡

ሁለተኛው የኢትዮ- ሱዳን የድንበር ጉዳዮች የከፍተኛ አመራር የፖለቲካ ውይይት በካርቱም ሁለተኛው የኢትዮ- ሱዳን የድንበር ጉዳዮች የከፍተኛ አመራር የፖለቲካ ውይይት በካርቱም ተካሄደ፡፡፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ በሱዳን ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ በማንሳቷ ሱዳን የተሻለ ዕድገትና ግንኙነት እንዲኖራት ያስችላል ብለዋል፡፡

በሱዳን ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ ዕውቅና መስጠት በሁሉም ዘርፍ ወደ ዕድገት የሚያሻግርና አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሱዳን ለሚካሄድ ለውጥ ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቷ ህዝብና መንግስት በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመረዳታቸውና በመደገፋቸው አቶ ደመቀ አመስግነዋል፡፡
በህግ ማስከበር ወቅት ድንበር አቋርጠው በሱዳን ለተጠለሉ ዜጎች የተደረገውን አቀባበልና ድጋፍም አድንቀዋል፡፡

በፌደራል መንግስት የተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በስኬት መጠናቀቁን አስረድተው፣ በክልሉ ሰላም መስፈኑን፣ መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ መልሶ ወደ ስራ የማስገባትና ሰብዓዊ ድጋፍ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡

በሱዳን ከተጠለሉት ውስጥ ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ መሆናቸውን አንስተው፥ ቀሪዎቹም በፍላጎታቸው ወደቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ወንድማማችና እህትማማች ህዝብ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ አብሮ ለማደግ ግንኙነቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ትስስርን በማጎልበት የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሰራለንም ብለዋል አቶ ደመቀ በንግግራቸው፡፡

ሃገራቱን ይበልጥ በትራንስፖርት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት በማስተሳሰር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ያሻልም ነው ያሉት፡፡

በዘርፉ ያለውን ትስስር ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ጋር የተደረገው ውይይት አስደሳች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በድንበር አካባቢ የሚካሄድ ንግድ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ በአካባቢው የሚኖሩ የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችልም አውስተዋል፡፡

በዚህ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ወደ ተግባር መግባት ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ፥ ከሀያ አመታት በፊት የተፈረመውን የድንበር ላይ ንግድ በማሻሻል ወደ ተግባር መቀየር አፍሪካ ለጀመረችው ነፃ የንግድ ቀጠና እንደ ጥሩ ምሳሌ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት አንድም ሁለትም ናቸው፤ አንዱ ውስጥ የሰላም እጦት ቢኖር ጫናው አንደኛው ጋር መድረሱ አይቀርም፤ ሰሞኑን ድንበር አካባቢ ያጋጠመው ችግርም ይህንን ያላገናዘበ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ሳምንታ አካባቢ ጀምሮ ድንበር ላይ የሱዳን ጦር በከባድ መሳሪያዎች በመታገዝ ጥቃት ሲፈፀም መቆየቱን በመጥቀስም የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ምርት መዘረፉን እና ሰላመዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ጉዳዩን በትኩረት እየተመለከተው እንደሚገኝ በማስረዳት ችግሩን በመነጋገር መፍታት ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ባለፈው ግንቦት ወር የድንበር ጉዳይን አስመልክቶ አዲስ አበባ ላይ ውጤታማ ውይይት መደረጉን አስታውሰው፥ በዚህ መሰረት ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለችግሩ የጋራ መፍትሄ በማመንጨት በዘላቂነት መፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል፤ ግጭትን ማባባስ ሁለቱን ህዝቦች እና ሀገራት የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም እንደማይሆን በመጥቀስ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን መልካም ጉርብትና በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.