Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የመሠረተ-ልማት ዕድሎች የሚያስተዋውቅ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 11፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመሰረተ-ልማት እድሎች ለቻይና ኩባንያዎች የሚያስተዋውቅ ፎረም በዌቢናር አካሄደ።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መንግስት ለመሰረተ-ልማትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

መድረኩ በዘርፉ ፖሊሲዎች፣ የቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው ጉዳዮች እና በኢትዮጵያ በዘርፉ መሰማራት በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

አያይዘውም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ መጠን ለማሻሻልና ለመለወጥ የመሰረተ-ልማትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

ቻይና በዘርፉ ካላት ሰፊ ልምድና የቴክሎኖጂ አቅም አኳያ ኢትዮጵያ ብዙ መጠቀም ትችላለች ያሉት አምባሳደሩ፥ ሚሲዮኑ ከቻይና ዓለም አቀፍ ተቋራጮች ማህበር ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በዘርፉ የተሰማሩ የቻይና ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ይሰራል ብለዋል።

ለወደፊቱም የግሉ ዘርፍ በዚህ ረገድ የመሪነት ሚና እንዲወስድ ማድረግ የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ነው ማለታቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ኢትዮጵያና ቻይና በትራንስፖርትና ሎጂስቲክሱ ዘርፍ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ውጤታማ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማድረጋቸውን አውስተዋል።

ለዚህም በስኬት ተጠናቆ በስራ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ነው ያነሱት።

መንግስት በአስር አመቱ የልማት ዕቅድ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በወደብ፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በአቪዬሽን፣ በሎጂስቲክስ ከተማ ግንባታና በተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ልማት ላይ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ከቻይና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደምታገኝ በመጠቆም፥ መንግስት ለማምረቻው ዘርፍ ፣ ለግብርና እና ለግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

አክለውም በኢትዮጵያ ካለው ምቹ ሁኔታ አኳያ ቻይናውያን ባለሀብቶችና ኩባንያዎች መንግስት ትኩረት በሰጣቸው ዘርፎች በሀገሪቱ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሜ መንግስት የኢንቨስትመት ዘርፉን በይበልጥ ለማስፋትና የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደ ሃገር በርካታ ጫናዎችን በመቋቋምም በርካታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል ያሉት ኮሚሽነሯ፥ በኢትዮጵያ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ከቻይና ዓለም አቀፍ ተቋራጮች ማህበር ምክትል ሊቀ-መንበር ዢን ዢዩሚንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በፈረንጆቹ 2019 በእርሳቸው የተመራ የቢዝነስ ልዑክ በኢትዮጵያ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ የባቡር፣ የመንገድና የመሳሰሉ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎችን ማከናወናቸውን በመጥቀስም፥ ይህም ሁለቱ ሀገራት በዘርፉ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር እንደሚያመላክት አንስተዋል።

በማህበሩ ስር ያሉና በዘርፉ የተሰማሩ የቻይና ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በተለይ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በታዳሽ ሀይል ማመንጨትና በግብርናው መስኮች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተል።

በፎረሙ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም የቻይና ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን ጨምሮ ከ900 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.