Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የአለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደረጃን ለማሻሻል የዩኒቨርሲቲዎችን ሙሉ አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 16 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያን የአለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ደረጃን ለማሻሻል የዩኒቨርሲቲዎችን ሙሉ አቅም  መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያለውን የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ዝግጁነት የዳሰሳ ጥናት አቅርቧል።

በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ሃዋሳና አዳማ ከተሞች እንዲሁም በየከተሞቹ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ደረጃ አጥንቶ ክፍተቶችን ለይቷል።

በዚህም በዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ መሰረተ ልማትና የሰው ሃይል መኖሩን ቡድኑ ያረጋገጠ ሲሆን÷ የአይሲቲ ዲፓርትመንት የሌላቸው የከተማ አስተዳደሮች መኖራቸውንም  አመላክቷል።

በአዲስ አበባ የተሻለ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ጅማሮዎች ሲኖሩ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በተናጠል ጅምር ስራዎች መኖራቸው ተገምግሟል።

ሁለት ክልሎችን እያስተናገደ ያለው የሀዋሳ ከተማ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሰራቸውን ስርዓቶች በከተማዋ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን ገምግሟል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተነሳሽነትና በቢሮ ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች ሲኖሩ እነዚህን ወደ ከተማ ማስፋት ይጠይቃል ተብሏል።

ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ችግር አለበት የተባለው የአዳማ ከተማ አስተዳደር የነዋሪነት መታወቂያ ዲጂታል ማድረግና የጋብቻ ቅፅን ኦንላይን መስጠት የመሳሰሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛልም ነው ያለው።

በሁሉም ከተሞች የመሰረተ ልማት ችግርና የአቅም ግንባታ ክፍተቶች መኖራቸው ተለይቷል።

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ መሰረተ ልማት ሲኖራቸው ሲስተሞችን በማልማት ወደ ገበያ ጭምር ያወጡ መኖራቸውም ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በመሰረተ ልማትና በሰው ሃይል የተሻለ አቅም ስላላቸው አቅማቸውን አሟጦ  መጠቀም እንደሚገባ መጠቆሙን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኑ በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛ ጊዜና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ የሚችሉ ምክረ ሃሳቦችንም አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.