Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የግብፅ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሚኒስትሮች፣ የውኃ ዘርፍ እና የህግ ባለሙያዎች ዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተዋል።

የመጀመሪያው ቀን ውይይት የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር እና የአለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበት ነው የተካሄደው።

በዚህም በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የስምምነት ረቂቅ ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል።

የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የስምምነት ረቂቅ ከዚህ ቀደም በቴክኒክ ደረጃ በተደረጉ ድርድሮች የተገኘ ውጤትን መሰረት አድርጎ መዘጋጀቱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጠቅሰዋል።

ሶስቱ ሃገራት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከ10 ቀን በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ያካሄዱት ውይይት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም የሶስቱ ሃገራት የቴክኒክ እና የህግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የመጨረሻ የስምምነት ረቂቅ ለማዘጋጀት ባሳለፍነው ሳምንት በሱዳን ካርቱም መገናኘታቸው አይዘነጋም።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.