Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ እየተወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከትናንት ጀምሮ እየተወያዩ ነው።

ከዚህ ቀደም ሀገራቱ በደረሱት ስምምነት መሰረት ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ተገናኝተው በመወያየት ላይ የሚገኙት።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አተኩሮ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ የሀገራቱ የውሃ ሚኒስትሮችም እየተካፈሉ ሲሆን፥ የአሜሪካ መንግስት እና የዓለም ባንክ ተወካዮችም በታዛቢነት ተገኝተዋል።

ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ በተለያዩ ዙሮች የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ያደረጓቸውን ድርድሮች ውጤት ይመለከታሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ሲያካሂዱት የቆዩት አራተኛና የመጨረሻው የቴክኒክ ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ውይይቱ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ አዲስ ሃሳብ ይዛ በመቅረቧ መሆኑንም የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ግብፅ ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመት እንዲሞላ የሚል አዲስ ሀሳብ ማቅረቧ እና ኢትዮጵያ በበኩሏ ይህን ሃሳብ በማንኛውም መልኩ እንደማትቀበል መግለጿን ነው ሚኒስትሩ በወቅቱ የተናገሩት።

ሶስቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የህዳሴው ግድብ በ7 ዓመት ውስጥ እንዲሞላ ስምምነት ላይ ደረሰው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

ሶስቱ አገራት በዋሺንግተን ዲሲ በደረሱት ስምምነት አማካኝነት ስምምነት ላይ ካልደረሱ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በካርቱም የተፈረመው ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል።

የካርቱም ስምምነት አንቀጽ 10 “ሶስቱ አገራት በመርሆዎች ስምምነቱ አተረጓጎምና ተግባራዊነት የተነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ለአገራቸው መሪዎች ሊያሳውቁ ይችላሉ” ይላል።

ይህንንም የሚያደርጉት የሶስቱም ሀገራት ስምምነት ሲኖር እንደሆነም አስቀምጧል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.