Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን መረጋጋት እንዲፈጠር ለሁሉም ወገኖች ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግስት በካርቱም ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

በሱዳን እየተከናወኑ ያሉ ክስተቶችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት፥ ይህም በሃገራቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት ከኖረው ጠንካራ የወንድማማችነት ትስስር የመነጨ መሆኑን አንስቷል።

መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ከሲቪል እና ወታደራዊ አካላት የተውጣጣ ጥምር መንግስት እንዲመሰረት እና የሽግግር ጊዜ ህገ መንግስት ሰነድ እንዲዘጋጅ ጉልህ ሚና መጫወቱን አስታውሷል።

አሁን ላይም በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም የሚወስዳቸውን ማንኛውንም ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ ያደረገቸው ሽግግር የተሟላ እንዲሆን እንደሚደግፍና የሽግግር ዘመኑን ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ ሙሉ በሙሉ እንደሚያከብር ነው የገለጸው።

ኢትዮጵያ የሱዳን ሕዝብ ሉዓላዊ መብቶችና ፍላጎቶች እንዲከበሩ እና በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ማናቸውም የውጭ ጣልቃነት እንዳይኖር ማድረግ በእጅጉ እንደሚያስፈልግም በድጋሚ አስታውቃለች።

የሱዳን ህዝብ አሁን ያጋጠሙትን እነዚህን ተግዳሮቶችና ችግሮች ተቋቁሞ፣ በስተመጨረሻ ሰላማዊ መፍትሄ በሚያገኙበት መንገድና ጥበብ በተሚላበት አኳኋን እንደሚፈታቸው ያለውን ሙሉ እምነት የኢትዮጵያ መንግስት በመግለጫው አስረድቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ምንጊዜም ከሱዳን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት ጋር ጸንቶ እንደሚቆም ነው በመግለጫው ያረጋገጠው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.