Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድንና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ማገበያየት ሊጀምር ነው

 አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2014 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕድንና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ ሊያስገባ መሆኑን አስታወቀ።
በሁለት የግብርና ምርቶች የጀመረውን ግብይት አሁን ወደ 13 በማሳደግ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እያገበያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት ከግብርና ምርቶች ውጪ የማዕድን ምርቶችን ማገበያየት ይጀመራል፡፡
ኦፓል፣ ሳፋየርና ኤመራልድ የጌጣጌጥ ማዕድናት ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ እንደሚገቡና በቀጣይ ሌሎች የማዕድን ምርቶችን የማገበያየት እቅድ እንዳለም ነው የተገለፀው፡፡ የማዕድን ምርቶች በምርት ገበያው እንዲገበያዩ መደረጉ ሕጋዊ ስርዓትን የተከተለ ግብይት በመፈጸም ሕገ-ወጥ የማዕድን ሽያጭን ለማስቀረት ይረዳል ተብሏል፡፡
ምርት ገበያው በ2014 በጀት ዓመት ከማዕድን ምርቶች በተጨማሪ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓቱ እንደሚያስገባ ገልጿል፡፡ በዚህም ጥቁር አዝሙድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ እርድ፣ ኮረሪማና አብሽ እንዲሁም ከቅመማ ቅመሞች በተጨማሪ ጓያ፣ የዱባ ፍሬ፣ ሙጫ፣ ኦቾሎኒና ሩዝ ወደ ግብይት ስርዓቱ ይገባሉ መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.