Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ መሰረታዊ ጉዳዮች

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 30 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ሦስት የተለያዩ ሕጎችን ማለትም የምርጫ ሕግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሕግና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ-ምግባር ሕግን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ በመሆኑና ይዘቱም በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በዚች አጭር ፅሑፍ ሙሉውን መዳሰስ የሚቻል አይደለም፡፡
1. ምርጫ ምንድን ነው?
ምርጫ “ከበርካታ መብቶች ወይም መፍትሔዎች መካከል አንዱን የመምረጥና ሌላውን የመተው ሂደት ወይም አንድን ግለሰብ የፖለቲካ ስልጣን እንዲይዝ የሚደረግ የመምረጥ ሂደት ነው” ይላል፡፡
የአገራችን ሕግ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አን. 2(5) ላይ “በፌደራልና በክልል ሕገ መንግስታት እንዲሁም አግባብ ባላቸው ሕጎች መሰረት የሚካሄድ የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ወይም የድጋሚ ምርጫ” መሆኑን ተደንግጓል፡፡
ከዚህም በመነሳት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ዜጎች ተወካዮቻቸውን፣ የሕግ አስፈፃሚውንና የሕግ ተርጓሚውን አካል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንግድ የሚቆጣጠርላቸውን እንዲሁም የሚተዳደሩበትን ሕግ የሚያወጣላቸውን ከሶስቱ የመንግስት አካላት አንዱ የሆነውን የሕግ አውጪ አካል የሚመርጡበት የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀር ሥርዓት ፓርላመንታዊ በመሆኑ (የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት አን. 45) እንደሌሎቹ በፕሬዝደንታዊ የመንግስት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ ሀገራት (ለምሳሌ አሜሪካ) መሪዎቻችንን በቀጥታ አንመርጥም፡፡
ሕዝቡ ተወካዮቹን ወይም የምክር ቤት አባላቱን ከመረጠ በኋላ በሕዝቡ ድምፅ መሰረት መንግስት የሚመሰርተው አሸናፊው የፖሊቲካ ድርጅት በፌደራል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስተሩን በክልሎች ደረጃ ደግሞ የክልሉን ርእሰ መስተዳድር ይመርጣል፡፡
የአስፈፃሚ አካሉንም ቢሆን በጠቅላይ ሚኒስቴሩና በክልል ርእሳነ መስተዳድሮች አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ሹመታቸው ይፀድቃል እንጂ ሕዝቡ በቀጥታ የሚመርጥበት ሥርዓት የለም፡፡
2. የምርጫ ሥርዓት፣ መርሆዎችና ዓይነቶች (አ/ቁ 1162/11 ከአንቀፅ 4-11)
በዓለማችን ላይ በዋናነት የሚታወቁት የምርጫ ሥርዓቶች የአብላጫ ድምፅ ውክልና የምርጫ ሥርዓትና የተመጣጣኝ ድምፅ ውክልና የምርጫ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ የአብላጫ ድምፅ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በሁለት ይከፈላል፡፡
የአብላጫ ድምፅ ውክልና (Simple Majority or First Past the Post) የቀደመ ሁሉንም ጠራርጎ የሚወስድበት የምርጫ ሥርዓትና ፍፁም አብላጫ ድምፅ ውክልና (Absolute Majority) ለማሸነፍ ከመራጩ ውስጥ ከግማሽ በላይ ድምፅ ማግኘት የሚያስፈልግበት የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡
የተመጣጣኝ ድምፅ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የሚባለው ሥልጣን ወይም የምክር ቤት መቀመጫ በመቶኛ መያዝ የሚያስችል የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ ሀገራችን የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምፅ ውክልና የምርጫ ሥርዓት መሆኑን በሕገ-መንግስቱ አን. 54(2) እና በአ/ቁ. 1162/11 አን. 4(1) ሥር ተደንግጓል፡፡
መሰረታዊ የሆኑ የምርጫ መርሆዎች መረጋገጥና መከበር ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መለኪያዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በሀገራችን የሚከናወን ምርጫ እነዚህን መርሆዎች መሟለት ያለበት መሆኑን በሕገ-መንግስቱ አን. 54(1) እና በምርጫ ሕጉ አን. 5 ላይ ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልፅበት እና ያለምንም ልዩነት በሚደረግ ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ ይሆናል በሚል ተደንግጓል፡፡
ዓይነቶቹን በተመለከተ በሕግ እውቅና የተሰጣቸው የምርጫ ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
(1) ጠቅላላ ምርጫ፡- በየአምስት አመቱ የሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ነው፡፡
ይህ የምርጫ በመሰረታዊነት በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ በተለያየ ጊዜ ሊካሄድም ይችላል፡፡
በዚህ የምርጫ ዓይነት የፌደራል የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት ከአንድ የምርጫ ክልል 1 ተወካይ ብቻ የሚመረጥ ሲሆን የክልል ምክር ቤቶች አባላት ደግሞ እንደየክልሎቹ የምክር ቤት አባላት ብዛት ከአንድ በላይም ሊመረጥ ይላል፡፡
አንድ ክልል ለፌደሬሽን ምከር ቤት የሚልካቸው አባላት በቀጥታ በሕዝቡ እንዲመረጡለት ከፈለገም ምርጫው አንድ ላይ ይካሄድለታል፡፡
(2) የአካባቢ ምርጫ፡- ይህ የመርጫ ዓይነት በየደረጃው የሚካሄድ የብሔረሰብ ዞን፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡
(3) የማሟያ መርጫ፡- ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በተለያየ ምክንያት የተጓደሉባቸውን አባላት እንዲሟሉላቸው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ የምክር ቤት አባል የይውረድልን ጥያቄ ሲቀርብ ተጣርቶ ተቀባይነት ሲያገኝ የጎደሉትን አባላት ለማሟላት የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡
(4) ድጋሚ ምርጫ፡- የምርጫ ቦርድ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የምርጫ ውጤት እንዲሰረዝና ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን ወይም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ መደገም ውጤት የሚያስከትል ውሳኔ ሲወስን እንዲሁም ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ ሲያገኙ አሸናፊውን ለመለየት ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት የምርጫ ዓይነት ነው፡፡
(5) ሕዝበ ውሳኔ፡- በሕግ መሰረት አግባብ ባለው አካል ሲወሰን የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት ወይም ለመወሰን የሚደረግ የምርጫ ዓይነት ነው፡፡
3. ስለመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባመራጮች እና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ሂደት የምርጫ አፈፃፀም ዋነኛ ተግባራት ናቸው፡፡
መምረጥና መመረጥ የሁሉም ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ቢሆኑም መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ደግሞ አሉ፡፡
አንድ ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
ዜግነቱ ኢ/ዊ መሆን ይገባዋል፣ ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፣ በምርጫ ክልሉ ቢያንስ 6 ወር የኖረ መሆን ይገባዋል፡፡
ቢሆንም የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው በሕግ የታገደባቸው ሰዎች ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ቢያሟሉም እንኳን በመራጭነት መመዝገብ አይችሉም (አንቀፅ 18)፡፡
አንድ መራጭ በአንድ ምርጫ ጣብያ ከአንድ ጊዜ በላይ ወይም በሌላ ምርጫ ጣብያ በድጋሚ መመዝገብ አይችልም (አንቀፅ 24)፡፡
የመራጮች ምዝገባ እንደተጠናቀቀም የመራጮች መዝገብ በምርጫ ጣብያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለ10 ቀናት ይፋ ወጥቶ ሕዝብ በግልፅ እንዲያየው መደረግ አለበት፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ለዕጩነት የሚያበቁ መመዘኛዎችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ፣ ዕድሜው 21 ወይም ከዚያ በላይ የሆነ፣ በምርጫ ክልሉ ለ1 ዓመት በቋሚነት የኖረ ወይም የትውልድ ቦታው በዕጩነት ሊቀርብበት በፈለገበት የምርጫ ክልል ውስጥ የሆነ፣ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልታገደ፣ የአእምሮ ሕመምተኛ ያልሆነ፣ የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብን ተቀብሎ የፈረመ መሆን ይገባዋል፡፡
ከዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ የደህንነት ሰራተኞችና የምርጫ ቦርድ ሰራተኞች ውጪ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በግል ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆን ለምርጫ መወዳደር የሚችሉ ሲሆን በምርጫ ቅስቀሳ እና ምርጫው በሚከናወንበት ጊዜ ማንኛውንም የመስሪያ ቤቱን ንብረት ሳይገለገሉ ያለደመወዝ ፈቃድ ይሰጣቸዋል (አንቀፅ 33)፡፡
መረጃው የጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.