Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 2 ቢሊየን ብር ለጥቃቅንና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት እንዲደርስ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በልማት ባንክ በኩል 2 ቢሊየን ብር ለጥቃቅንና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት እንዲደርስ ማድረጉን ገለጸ።

አሁን ላይ መንግስት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የንግድም ይሁን የማምረቻ ኢንዱስትሪው ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ከኮቪድ19 ጋር ተያይዞ የወጪና ገቢ ምርቶች እንዳይቀዛቀዙ በብሄራዊ ባንክ በኩል በርካታ ስራ መሰራቱን የብሄራዊ ባንከ ምክትል ገዥ ዋና ኢኮኖሚስት ፍቃዱ ድጋፌ ይናገራሉ።

በዚህም የአበባ ላኪዎች በአስገዳጅነት የሚገቡትን ዝቅተኛ የዋጋ ኮንትራት ለሶስት ወር ማንሳት እንዲሁም ከኮቪድ19 ጋር ተያይዞ ለሚገቡ ምርቶች እና ጥሬ እቃዎች ባንኮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያስተናግዱ መመሪያ መሰጠቱን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ለላኪዎች የሚሰጠው የ5 ሺህ ዶላር ቅድሚያ ክፍያ ወደ 50 ሺህ ከፍ እንዲል መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም አስመጪና ላኪዎች ያልተወራረዱ የውጭ ምንዛሬዎችን ከባንኮች ወደ ብሄራዊ ባንክ በመላክ ያወራርዱበት የነበረውን አሰራር በማስተካከልና የሰው ንክኪን ለመቀነስ በሶስት ወር በባንኮቹ እንዲሰራ አድርጓልም ነው ያሉት።

የዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ ለመቀጠል እና ባንኮች በኮቪድ19 ምክንያት ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸውም ለግል ባንኮች 15 ቢሊየን ብር እንዲሰጥ ተደርጓል።

በቅርቡ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ ለተጎዳው ቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ባንኮች በአመት ውስጥ መክፈል የሚችሉት አምስት ከመቶ ወለድ እንዲያገኙ ተደርጓልም ነው ያሉት።

መንግስት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያከናወነ ካለው ማህበራዊ የጤና ክንውኖች ባሻገር በጥቃቅንና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በልማት ባንክ በኩል 2 ቢሊየን ብር ለጥቃቅንና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን አስረድተዋል።

እርምጃው መንግስት የዜጎቹን ደህንንት በመጠበቅ የፋይናንስ ዘርፉን በመደገፍ ኢኮኖሚውን ለመታደግ እየሰራ ያለው ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ መልኩ ዜጎችን ለመታደግና ኢኮኖሚውን ለማንሳት በሚደረግ ጥረትም የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ ከፍ ሊል እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.