Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሁለት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ውይይት አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመቀነስና በምርጫ ሂደት ላይ ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብሩ የፀጥታ አስከባሪ አካላት የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር ድንጋጌዎች ላይ መክሯል።

የመጀመሪያው የውይይት መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከጤና ባለሞያዎች፣ ከፓለቲካ ፓርቲዎችና ከፀጥታ አካላት ጋር የተደረገ ሲሆን፤ ቀጣዩና በዛሬው ዕለት ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገው ውይይት ደግሞ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጎ ውሏል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ መመሪያዎቹ በምርጫ ወቅት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ስለሚኖር የኮቪድ 19 ሥርጭትን መቀነስ ለማስቻል፣ ከሁሉም ወገን ምን ይጠበቃል የሚለውንና ይህም ሲሆን የመራጩንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ላይ ጫና በማያሳድር እንዲሁም የአስፈጻሚ አካላትንና የታዛቢዎችን መብት ባከበረ መልኩ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች የሚገኙ ግብዓቶችን አስፈላጊነት የገለጹት ብርቱካን ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት መመሪያዎች ለማዘጋጀት የተሣተፉትን የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሞያዎችንም አመስግነዋል።

የመጀመሪያውን ቀን ውይይት የመሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ የሁለተኛውንና በዛሬው ዕለት የተደረገውን ውይይት ደግሞ የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ መርተውታል።

በሁለቱም ቀን ውይይቶች ላይ የቦርዱ የሕግ ክፍል ባልደረባ በሆኑት ወንጌል አባተ አማካኝነት መመሪያዎቹ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበት መድረኩ ለተሳታፊዎች ክፍት የተደረገ ሲሆን፤ ከመድረኩም ሁለቱም መመሪያዎች ላይ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

ለመጀመሪያው ቀን ውይይት ከመድረኩ ለተሰጡት አስተያየቶች በሕግ ባለሞያው ወንጌል አባተ፣ የምርጫ ቦርድ የኮቪድ 19 አስተባባሪ በሆኑት ዶ/ር ኢማን አብዱልሀኪምና በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በዛሬው ዕለት ከመድረኩ ለተነሡት አስተያየቶች በአቶ ወንጌል አባተና በዶ/ር ኢማን አብዱልሀኪም አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በሁለቱም ቀን ውይይቶች በተደረገው ሁለተኛ ዙር ምክክር፤ በቦርዱ ማቋቋሚያ ዐዋጆ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲሁም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምገባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 163 ንዑስ አንቀጽ 2 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በወጣው የምርጫ ፀጥታ አስከባሪ አካላት የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር መመሪያ ላይ በሕግ-ባለሞያው ሰለሞን ግርማ አማካኝነት ሠፊ ገለጻ የተሰጠበት ሲሆን፤ ገለጻውን ተከትሎ ከመድረኩ ሀሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

በመድረኩ መመለስ የሚችሉትን አስተያየቶች በሰለሞን ግርማ አማካኝነት መልስ ተሰጥቶባቸውና ግብዓት ተሰብስቦ ፕሮግራሞቹ መጠናቀቃቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.