Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ፣ የሶማሌ እና የደቡብ ክልሎችን የምርጫ ውጤት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በሐረሪ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች የተካሄደውን አጠቃላይ የምርጫ ውጤት አስመልክቶ መግለጫ አወጣ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባወጣው መግለጫ በመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ በአጠቃላይ ከተመዘገቡ 6 ሚሊየን 562 ሺህ 534 መራጮች መካከል 5 ሚሊዮን 914 ሺህ 670 ዜጎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይህም የመራጮች የድምፅ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 85 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤቶችን ለማረጋገጥ በህግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በይፋ የተረጋገጠውን ውጤት ማስታወቁን ገልጾ፣ ለምርጫው መሳካት በሂደቱ ለተሳተፉ ዜጎች፣ ትብብር ላደረጉ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፣ የፀጥታ ተቋማት እንዲሁም በተለያየ ደረጃ በምርጫ ሥራው ለተሳተፉ አስፈጻሚዎች ከፍተኛ ምስጋናውን አቅርቧል።

በቦርዱ በይፋ የተረጋገጠው የየአካባቢው የምርጫ ውጤት ማስታወቂያም ከመግለጫው ቀጥሎ ተያይዞ ቀርቧል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው:-

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአብዛኛው ምርጫ ክልሎች እና መቀመጫዎች 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ያከናወነ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች የተነሣ ምርጫ ባልተከናወነባቸው ሌሎች ምርጫ ክልሎች ደግሞ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ተከናውኗል።

በዚህ ሂደትም የመራጮች ምዝገባ ልተከናወነባቸው እና ባልተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ከነሐሴ 26 – ጷግሜ 05 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራጮች ምዝገባ እንዳከናወነ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት 6,562,534 (ከሕዝበ ውሣኔን ሳይጨምር) ያህል መራጮች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተከናወነው ምርጫ ላይ ለመሣተፍ ተመዝግበዋል።

በዚህ ሂደትም መራጮች እንዲመዘገቡ እና እንዲመርጡ አምስት መልዕክቶች በ11 ቋንቋዎች እና በስድስት ሚዲያዎች ተዘጋጅተው ለመራጮች የደረሱ ሲሆን፣ የመራጮች ትምህርት የመንገድ ላይ መረጃ መስጠት ዘመቻዎችም ምርጫ በሚከናወንባቸው ምርጫ ክልሎች ተከናውነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለፓለቲካ ፓርቲዎች በዘጠኝ ሚዲያዎች አጠቃላይ 123 ሰዓት የቴሌቨዥን እና ሬዲዮ ነፃ የዐየር ሰዓት ድልደላ ተከናውኗል።

ለሥልጠና፣ ለመራጮች ምዝገባ እና ለድምፅ አሰጣጥ በሦስት ዙር ሠፊ የቁሳቁሶች ሥርጭት የተከናወነ ሲሆን 9,874 የቁሳቁስ ኪቶች (ሰማያዊ ሳጥኖች) ተሰራጭተዋል። የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ከሀገር ውጪ የታተሙ ሲሆን ያለምንም ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ወደ ምርጫ ጣቢያ መድረስ ችለዋል። የመራጮች ምዝገባ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ለማስፈጸም 21,198 ያህል አስፈጻሚዎች የተሠማሩ ሲሆን በሁለት ዙር ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል።

በአጠቃላይም 5,935 (ከሕዝበ ውሣኔ ጣቢያዎች ውጨ) ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለ47 የተወካዮች ምክር ቤት እና 106 የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ተከናውኗል። በዕለቱም በአጠቃላይ ከ11 ድርጅቶች የተወጣጡ 2,569 ያህል የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች ሂደቱን ታዝበዋል።

የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ተጠናቆ በየምርጫ ክልሉ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ የቦርዱ የውጤት ማረጋገጫ ማዕከል በተጨማሪ ውጤቶችን በሕጉ መሠረት ለማረጋገጥ ሲሠራ ቆይቷል።

በዚህ ሂደትም ፓርቲዎች እንዲሁም ዕጩዎች የምርጫው ሂደት ላይ አቤቱታ ካላቸው ለቦርዱ እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን በዚህም መሠረት ስድስት ያህል ፓርቲዎች እና 24 የግል ዕጩዎች አቤቱታቸውን አቅርበዋል። በቦርዱ የሕግ ክፍል አቤቱታዎችን በማጣራት የሠነድ እና የሰው ማስረጃዎችን በማጠናቀር ዐይቶ ለውሣኔ ግብዓት አንዲሆን ሰርቷል።

ቦርዱ የውጤት ማጣራት ሂደትን ለማጠናከር እና የውጤት ድመራ እና ቆጠራ ጥራትን ለማረጋገጥ በሶማሌ ክልል በ33 የምርጫ ክልሎች (በሦስት ተወካዮች ምክር ቤት እና 30 የክልል ምክር ቤት) ከተሰጡት ድምፆች ላይ 10 በመቶው ድምፅ በምርጫ ክልል ደረጃ በድጋሚ እንዲቆጠር ወሥኖ በዚሁ መሠረት ተግባራዊ ተደርጓል።

በተጨማሪም የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ምርመራ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ዛሬ የሚገለጸው ውጤት ላይ ሳይካተቱ ቀርተዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት እና ተወካዮች ምክር ቤት

– ቡሌ
– ምስቃንና ማረቆ 2
– ሎሞ 01

በሶማሌ ክልል በክልል ምክር ቤት

– ጅጅጋ ከተማ
– ሙዩሙሉቄ

በመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ድምጽ አሰጣጡ በአጠቃላይ ከተመዘገቡ 6,562,534 መራጮች መካከል 5,914,670 ዜጎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህም የምርጫ ቀን የድምፅ መስጠት ተሣትፎ (voter turnout) 85 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዐዋጅ 1133/ 2011 አንቀጽ 07 ንዑስ አንቀጽ 18 ውጤቶችን ለማረጋገጥ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በይፋ የተረጋገጠው ውጤት ከሥር የተያያዘው መሆኑን እየገለጸ ለምርጫው መሳካት በሂደቱ ለተሣተፉ ዜጎች፣ ትብብር ላደረጉ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፣ የፀጥታ ተቋማት እንዲሁም በተለያየ ደረጃ በምርጫ ሥራው ለተሣተፉ አስፈጻሚዎች ከፍተኛ ምስጋናውን ለማቅረብ ይወዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ጥቅምት 02 ቀን 2014 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.