Fana: At a Speed of Life!

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የክፍያ ስርዓት መመሪያ አወጣ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የክፍያ ስርዓት መመሪያ  ማውጣቱን አስታወቀ፡፡

አዲሱ መመሪያ አሁን ያለውን የክፍያ ስርዓት ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሏል፡፡

ለክፍያ መሳሪያዎች አቅራቢዎች ፈቃድና ስልጣን የሚሰጠው ይህ መመሪያ ከመጋቢት 23 ጀምሮ  ስራ ላይ እንደሚውል ብሔራዊ ባንኩ ገልጿል።

በባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተፈርሞ የጸደቀው መመሪያ÷ የክፍያ መሳሪያዎችን ፈጠራ በማበረታታት፣ የፋይናንስ አገልግሎትን በማቀላጠፍና በማሳደግ ረገድ ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል።

መመሪያው ግልጽና አስቻይ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት የሚፈልግና የክፍያ መሳሪያዎቹ የተገልጋዮችን ፍላጎት የሚያስጠብቁ ናቸው ብሏል፡፡

ፈቃድ ካላቸው ተቋማት ውጭ የክፍያውን መሳሪያ ለማግኘት የሚፈልግ አካል በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት ፈቃድ ማግኘት እንደሚችሉም ብሄራዊ  ባንኩ   አመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት በባንኩ የተረጋገጠ ፈቃድ የተሰጣቸው የክፍያ መሳሪያው አቅራቢዎች ገንዘብ ወጪና ገቢ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ ሃዋላን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ያስችላልም ነው የተባለው።

በብሔራዊ ባንኩ በተሰጠ የጽሁፍ ፈቃድ መሰረት የክፍያ ስርዓቱ አቅራቢዎች አገልግሎታቸውን ለሌሎች በውክልና ሊሰጡ እንደሚችሉ በመመሪያው  መቀመጡ ተገልጿል፡፡

የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ስጋት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ለመከላከል ሲባል ብሔራዊ ባንኩ የክፍያ ስርዓቱ አቅራቢዎችን፣ ወኪሎችና ሌሎች አብረው የሚሰሩ አካላትን እንደሚቆጣጠር መመሪያው ማስቀመጡን ኢ.ዜ.አ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.