Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን  21ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን  21ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን  አካሄደ።

በጉባኤው የ2012 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም፣ የኦድት ሪፖርት፣ የ2013 በጀት አመት እቅድ እና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

በቀረበው ሪፖርት እንደተመላከተው በዞን አምስት፣ በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን፣ በአለም አቀፍ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ደረጃ እና ከአቻ ፌዴሬሽኖች ጋር ያለው አለም አቀፋ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተገልጿል።

የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት አሰራር ተተኪን ስፖርተኞች ከማፍራት አንፃር ክፍተት ያለበት በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የጉባኤው አባላትም በጉባኤው አጀንዳዎች ውይይት ያደረጉ ሲሆን የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ፕሮጀክት  ተተኪዎችን ከማፍራት አንፃር  ጥናት ላይ ተመስርቶ መሠረት ያለው ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየት ሰጠዋል።

የክልል ፌዴሬሽኖች  ለስፖርቱ  እድገት እስከታችኛው የስፖርት  አደረጃጀት ድረስ መስራት እንዳለባቻው፣ የፈረሱ ክለቦችን መልሶ መቋቋም እንደሚገባ እንዲሁም በሁለቱም ፆታ የክለቦች ተሳትፎ መጨመር እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የዳኞች የአሰልጣኞች እና የአመራሩን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ በጉባኤው ተሳታፊዎች  ተነስቷል።

በጉባኤው  የሽልማት እና የስራ አስፈፃሚ መተዳደሪያ መመሪያ  ጉባኤው ቀርቦ  ሊስተካከሉ ይገባል ያላቸውን ግብአቶችን በማካተት አፅድቆታል፡፡

የሽልማት መመሪያውም በውጭ ሀገር ውድድሮች እና በሀገር ውስጥ ውድድሮች ተሳትፎና ውጤታማነት ላይ መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት  አስተያየት ተሰጦበታል፡፡

በመጨረሻም በቀጣይ 4 አመታት ፌዴሬሽኑን የሚያገለግል የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፥ አቶ መስፍን አበራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አድርጎ በመምረጥ እና 6 የስራ አስፈፃሚ አባላትን በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.