Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
 
ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ከመንግስት የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ከሪል ስቴት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ፈላጊዎችን ከተለያዩ አካላት ጋር በማቀናጀትና ማህበር በመመስረት የቤት ፍላጎትን ለማሟላት ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥናትና የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን የነበረ ተቋም ነው ተብሏል፡፡
 
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቤት ፈላጊዎችን ምዝገባ፣ ክፍያ የመሰብሰብና ሌሎችንም የፋይናንስ ሥራዎች ባንኩ ባለው አሰራር መሰረት ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር እንደሚሰራ ተቋሙ ሥራ መጀመሩን በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ይፋ ባደረገበት ሥነ ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡
 
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመገናኛ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ከመንግስትና ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አስታውሰው፣ አሁንም የተለየ ሃሳብና አማራጭ ይዞ ከመጣው ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር ለመስራት መስማማቱን ተናግረዋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ሥራ አስኪያኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ይዞት የቀረበው ሓሳብ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ አካላትን ያቀናጀ አዲስ አማራጭ በመሆኑ ባንኮችና የተለያዩ አካላት ሥራውን መደገፋቸው ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
የጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አልማው ጋሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለበርካታ ሃገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ከሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ በዚህ ሃሳብ ላይ የሚሰጠው ድጋፍ ዜጎችንና ሃገርን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
 
ፕሮጀክቱ ዜጎች የቤት ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንዲቆጥቡ የሚያበረታታ መሆኑንና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አቶ አልማው ጠቁመዋል፡፡
 
ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በአራት የተለያዩ ሳይቶች የአርክቴክቸራል ዲዛይን ሥራ በማከናወን አንድ ሺህ የሚደርሱ ቤቶችን ለማስገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
 
በያዝነው ዓመት 10ሺህ ቤቶችን እንዲሁም በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 100ሺህ ቤቶችን ለማስገንባት ማቀዱንም ገልጿል፡፡
ቤት መገንባት የሚሹ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ቅድሚያ ክፍያ 350ሺህ ብር ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር በሚኖራቸው ስምምነት የመመዝገቢያ ቅድሚያ ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዝግ ሂሳብ ገቢ በማድረግና ማህበር በመመስረት የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡
 
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ ጋር ቤት ለመገንባት ስምምነት ላይ የደረሱ ቤት ፈላጊዎችን ምዝገባ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
 
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.