Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ‹ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው ስለማይስማሙ የፈለግኩትን እፈጽማለሁ› ብሎ በእብሪት የመጣን ጠላት አሳፍረው የመለሱበት ነው- አፈ ጉባኤ አደም

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበትና ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ አስጠብቀው ለተተኪው ትውልድ ያስተላለፉትን ጀግኖች የምንዘክርበት  80ኛው የአርበኞች የድል ክብረ በዓል ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩ ትርጉም አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ገለፁ።

ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰበቦችና ሕዝቦች ለ80ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢትዮጵያ አርበኞች  ቀን እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው ይህች ዕለት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብዝኃነታቸው አጥር ሆኖ ሳይለያያቸው፣ የሐሳብ ልዩነት ሳይነጣጥላቸው አገርንና ሕዝብን ለመታደግ ባህር ተሻግሮ፣ ጦር ሰብቆና ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ታጥቆ የመጣን ወራሪ ጠላት በአንድነት ተሰልፈው በመፋለም የአሸናፊነት አክሊል፣ የአይበገሬነት ቀንዲልና ዘላለማዊ ድል መቀዳጀታቸውን ለዓለም ሕዝብ የአበሰሩባት ናት ብለዋል፡፡

በዚያውም ለጥቁር ሕዝቦችም ለነጻነታቸው ለመታገል የ‹ይቻላል› መንፈስ እንዲላበሱና የአሸናፊነት ወኔ እንዲሰንቁ መልዕክት የተላለፈበት ዕለት መሆኑን አስፍረዋል፡፡

በዚያ ለነጻነት በተከፈለ የተጋድሎ ታሪክና የአርበኝነት ዘመን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንዳቸው ለሌላቸው መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ክቡር ሕይወታቸውን ለሚወዷት አገራቸውና ወገናቸው ገብረዋል ነው ያሉት፡፡

በፈሰሰው ደማቸውና በተከሰከሰው አጥንታቸውም ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ አስጠብቀው ለተተኪው ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም በነፋስ አመጣ ወሬ ሳይታለል፣ በወፍ ዘራሽ የሀሰት ትርክት ሳይደለል በስሜት ሳይሆን በስክነት፣ በልዩነት ሳይሆን በአንድነት፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፣ በመራራቅ ሳይሆን በመደመር መንፈስ የተጀመረውን የአንድነትና የብልጽግና ጉዞ በማስቀጠል ሀገሪቱን በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ የአፍሪካ ኩራትና የሥልጣኔ ሰገነት ለማድረግ ቀን ከሌሊት ሊታትር ይገባል በማለት ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን ‹ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳቸው ስለማይስማሙ የፈለግኩትን እፈጽማለሁ› ብሎ በእብሪት የመጣን ጠላት አሳፍረው የመለሱበት ነው፡፡

የዚያ ዘመን ትውልድ ታሪክ የሚዘከረው፣ ዘመን የማይሽረው ድል የተቀናጁት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ለአንድ ዓላማ ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድነት በመቆማቸው ነው።ያ ዘመን ከአሁናዊው ሁኔታ ጋር በብዙ ነገር ይመመሳሰላል፡፡ አሁንም እንደዚያኑ ዘመን ታሪካዊ ጠላቶች ‹ኢትዮጵያ ተዳክማለች፤ የውስጥ አንድነታቸውተናግቷል› በማለት ከማሟረታቸውም ባሻገር የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ የኢትየጵያን መውደቅና የሕዝቦቿንም መንበርከክ ለማየት ሲማስኑ ውለው ያድራሉ ብለዋል፡፡

የቋመጡለትን ምኞታቸውን ወደ ቀቢጠ ተስፋነት ለመቀየርና ሕልማቸውን ለማምከን በብዝኃነት ላይ የተመሠረት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለሀገሪቱ በሁለንተናዊ መልኩ ዘብ መቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

አርበኝነት ለኢትዮጵያ ለዘመናት አብሯት የኖረ መለዮዋና መጠሪያዋም ነው፤ አርበኝነትን ከኢትየጵያዊነት፣ ኢትየጵያዊነትንም ከአርበኝነት መነጠል ከቶውንም አይቻልም፤ሁለቱም በኢትየጵያዊያን ልብ ውስጥ ውህድ ሆነው የሚኖሩ ናቸው፤ ሁለቱም ላይለያዩ የተጋመዱ በኢትየጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የታሪክ መዝገብ ውስጥ ታትመው ዘመናትን የተሻገሩ ናቸው በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የትላንት አርበኞች አባቶች ወራሪ ጠላትን መክተው የሀገሪቱን ዳር ድንብር አስከብረው የራሳቸውን አኩሪ የአርበኝነት ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፡፡

የዛሬው ትውልድም ጠላቱ የሆኑትን ድኽነትን፣ ጽንፈኝነትን፣ አግላይነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት የአባቶቹን የአርበኝነት ታሪክ መድገምና ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፈው የራሱንም ታሪክ መከተብ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

˝ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ጠላቶችን ለማሸነፍ ከመቼም ጊዜ በላይ  በአንድነት በመቆም ሕብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ለማናጋት የተሰለፉት ሃይሎች የምንታገልበት ጊዜና ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ከትናንቱ አንድነታችንና ድሎቻችን ተምረን ዛሬም በአገራችን ሉዓላዊነት ላይ የሚመጣ ጠላት በአንድነት መመከትና ለቀጣይ ትውልድ ታሪክ ማስቀመጥ ይኖርብናል˝ ብለዋል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.