Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሚያስገነባው ባለ 12 ወለል ሁለገብ ህንፃ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ753 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ለሚያስገነባው ባለ 12 ወለል ሁለገብ ህንፃ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ።

የመሠረት ድንጋዩን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አስቀምጠዋል።

አቶ ኤሊያስ ሽኩር በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት ፌዴሬሽኑ ለሚያስገነባው ህንፃ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ለሀገራችን ስፖርት እድገት ዋነኛው የፋይናንስ ችግር መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም እራሱን በፋይናን ለማጠናከር እና ከመንግስት ድጎማ ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረት ለሌሎች ስፖርት ማህበራት አርዓያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸናፊነት የምንታወቅበት መገለጫችን መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ይህ ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የህንፃው መገንባት የፌዴሬሽኑን የፋይናንስ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድግ እና አትሌቲክሱን አንድ እርምጃ ከፍ እንደሚያደርገው ገልፃለች።

የሚገነባው ሁለገብ ህንፃ የህክምና ማዕከል፣ ሙዚየም ፣ ጅምናዚየም ፣ ላይበራሪ ፣ ቢሮዎች እና ለሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.