Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር መከላከል ፣ በአዲስ ዲዛይን ያሰራውን መለያ አርማ እና ያስገነባውን አዲስ የአስፓልት መንገድ አስመረቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2013 (ኤ.ቢ.ሲ)  በኢ.ፌ.ዴ.ሪ  አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር መከላከል ፣ በአዲስ ዲዛይን ያሰራውን የምክትሉን መለያ አርማ እና ያስገነባውን አዲስ የአስፓልት መንገድ አስመረቀ፡፡

መለያ አርማውንና መንገዱን መርቀው በመክፈት የስራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ  አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር  ጀነራል ይልማ መርዳሳ ናቸው፡፡

አዛዡም በንግግራቸው ምክትሉ ለአየር ኃይሉ ውጤታማ የተልዕኮ አፈፃፀም ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አስታውሰዋል።

በተለይም በጁንታው ድንገተኛ ጥቃት የተበታተነውን የሰው ኃይልና የወደመውን የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን በፍጥነት መልሶ በማደራጀት የህግ ማስከበር ዘመቻችን በድል እንዲጠናቀቅ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡

አየር መከላከያውን  ለማዘመን በምክትሉ አመራሮችና አባላት ዘንድ አሁን የተጀመረው የስራ መነቃቃትና ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት  ዋና አዛዡ

አያይዘውም የአየር ኃይል ኮማንድም እንደ ሁል ጊዜው ለምክትሉ የሥራ አፈፃፀም የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር መከላከል ጊዜያዊ አዛዥ ኮሎኔል ኃይሉ መኮንን  በበኩላቸው ÷ አየር መከላከያ ካለበት የግዳጅ ቀጣና ስፋት አንፃር ሰፋፊ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ወቅታዊ ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ ሳይቶችን በመምረጥ ፣ የሰው ኃይል በማደራጀት ፣ በስልጠናና ጥገና በኩል በተሰራው አመርቂ ተግባር በአሁኑ ወቅት የምክትሉ የግዳጅ አፈፃፀም በሁሉም ረገድ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በእለቱም ህግ በማስከበር ዘመቻ የበኩላቸውን ለተወጡ ምክትሎች ፣ ምድቦችና መምሪያዎች እንዲሁም በስራ አፈፃፀማቸው ብልጫ ላመጡ የአርማ ስጦታና የእውቅና ሰርተፊኬት የተበረከተላቸው ሲሆን ÷ በአዲስ ዲዛይን የተሰራ የምክትሉ መለያ አርማ እና የአስፓልት መንገድ በአየር ኃይል ዋና አዛዥና ኮማንድ በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሚገኙ አራቱ ክፍሎች አንዱ የሆነው ምክትል አዛዥ ለአየር መከላከል ፣ በማዕከላዊ ፣ በሰሜንና በምዕራብ እስከ ህዳሴው ግድባችን ሰፊውን የሀገሪቱን ክልል በመሸፈን የ24 ሰዓት የአየር ክልሉን ጥበቃ የሚያከናውን ለአየር ኃይሉ  ዋነኛው ድጋፍ ሰጪ ክፍል መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-

https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.