Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመጀመሪያ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥራውን በይፋ መጀመር የሚያስችለውን ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በጉባዔው ላይ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

ጉባዔው የተለያዩ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር ጠንካራ የትብብር ጥምረት የሚፈጥሩበት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

በመድረኩ የሆልዲጉ ዝርዝር ዓላማዎች፣ ዕሴቶች እንዲሁም በዘርፉ የዓለም አቀፍ ኮርፖሬቶች መልካም ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡

በመርሐ-ግብሩ መሠረትም በግልጽነት፣ በልዩ ተሠጥዖ፣ ድርጅት በሚያልፍባቸው የዕድገት ደረጃዎች ፣ በንግድ ሥነ-ምግባር ፣ ዕሴት እና በመሳሰሉት ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ገለጻ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡

ጉባዔው ዓለም አቀፍ ታዋቂ የዘርፉ ምሁራንን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን እንዲሁም የኩባንያዎች ቦርድ አባላትን በአንድ ላይ ያገናኛልም ነው የተባለው፡፡

ሐሳብ ለመለዋወጥ እና ተሞክሮዎችን ለመውሰድ የሚረዱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አጠር ያሉ ንግግሮች ፣ ግለሰባዊ ምልከታዎች እንዲሁም የቡድን ውይይቶች እንደሚኖሩም ከሆልዲንጉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቋቋመው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሃብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብና ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓት በመፍጠር ከሃብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሣሪያ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.