Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እውነት እንደ ደመራው ብርሃን መድመቁ አይቀሬ ነው-ም/ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገራችንን እውነት ሊጋርዱና ሊያጠለሹ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ሙከራ ቢያደርጉም የኢትዮጵያ እውነት እንደ ደመራው ብርሃን መድመቁ አይቀሬ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የመስቀል ደመራን በዓል ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የመስቀል በዓል ኢትዮጵያን በዓለም ያስተዋወቃትና የቱሪዝም መስህብ በመሆኑ ትልቅ አስተዋዕኦ እያደረገ ያለ ሀገራዊ ሀብታችን ነው ብለዋል።

በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ መስቀል ጨለማን የገለጠ፥ የብርሃንን አሸናፊነት ያሳየ፤ አዲሰ ተስፋን ያበሰረ ከድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ብርሃን መገኘት ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።

መስቀሉም እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ሲል ውድ የህይወት ዋጋ የከፈለበት ሆኖ ሳለ፤ክፉዎች መስቀሉንና የመሰቀሉን ግማድ ለመደበቅ የቆሻሻ ክምር በመከመር የመስቀሉን ሃይልና የፈውስ ምንጭነት ለመሰወር ከንቱ ጥረት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል።

ነገር ግን በቆሻሻ ክምር ቢጋሩዱትም፣ መሰቀሉንም ከመገኘት ሊከለክሉም ሆነ እውነትን ሊሰውሩ እንዳልቻሉ አብራርተዋል።

ይህንን ከአገራችን አሁናዊ ሁኔታ ጋር በመስተያየትም የመሰቀሉን እውነት በቆሻሻ ክምር ሊጋርዱት እንደጣሩት ክፉዎች ሁሉ፥ የአገራችንን የኢትዮጵያን እውነት ሊጋርዱ፤ ሊያጠለሹና የውሸት ቆሻሻ ሊከምሩ እየተጉ ያሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ሙከራቸው ሊሳካ እንደማይችል በአጽንኦት ገልጸዋል።

የውጭ ሃይሎች ኢትዮጵያን እኛ ካላስተዳደርን እናፈርሳታለን ብለው ከተነሱት የእናት ጡት ነካሽ ከሆኑ ከሃዲዎች ጎን ቆመው ሊያንበረክኩን ቢሞክሩም ፣ የቆሻሻ ተራራን ንደው ከተቀበረበት ቆፍርው እንዳወጡት ጽኑዓን ሁሉ እኛም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ዋጋ እየከፈልን አገራችንን ከከበባት ሀሰት፣ ትዕቢትና ዘርፈ ብዙ ጫና እናላቅቃታለን ሲሉ ተናግረዋል።

ህዝቦቿ በጀመሩት የትብብርም አሸናፊ እንደሚሆኑም እናምናለን ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ታሽንፋለች ፣ የኢትዮጵያ እውነትም እንደ ደመራው ብርሃን መድመቁ አይቀሬ ነው ሲሉ አስመረውበታል ምክትል ከንቲባዋ ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.