Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የቻይናው ሲዲሲ ተባብረው እንደሚሰሩ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 16፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የቻይናው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (CDC) በጋራ ተባብሮ ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ያካሄዱ ሲሆን፥ በዚህም ሁለቱ ተቋማት በዋናነት በበሽታ ክትትል ስርዓት፣ በጤና መረጃ አያያዝ፣ በድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አስተዳደር፣ በምግብ ደህንነት፣ በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር፣ በዘመናዊ ላቦራቶሪ ግንባታና በመሳሰሉት ላይ በጋራ ተባብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ውይይቱን የመሩት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና ሁሉን-አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በሴኔጋሏ ዳካር ከተማ የተካሄደው የ8ኛው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል በጤናው ዘርፍ የሚደረግ ትብብር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ መሆኑንንም ነው አምባሳደሩ ያስታወሱት።

አክለውም ተቋማቱ በቀጣይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ግንኙነታቸውን በይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሩክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ እንዲሁም የቻይናው ሲዲሰ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጆርጅ ፉ ጋዎ በውይይቱ መሳተፋቸውን በቻይና ኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.