Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ማዕከል ተቋቋመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ‘የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ማዕከል’ በሚል በማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ወጣኝነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት መቋቋሙን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ሃብቷን በከርሰ ምድሯ አምቃ የምትኖር የፀጋዎች ምድር እንዲሁም የልጆቿን ህይወት መቀየር የሚችሉ የከበሩ ማዕድናት በከርሰ ምድሯ ይገኛሉ” ብለዋል።
“በየትኛውም ጫፍ የሚገኙ የከርሰ ምድርም ይሁን የገፀ ምድር ሃብቶቿን መርምረው በሚገባው መጠን እንድትጠቀም አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ የሚያበለፅጓት ደግሞ የከበሩት ሃብቶቿ ውድ ልጆቿ ናቸው” ነው ያሉት።
ለዚህም “ልጆቿ በእውቀት መደገፍ አለባቸው” ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህ ውጥን የመጀመሪያው እርምጃ ደግሞ ‘የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ማዕከል’ በሚል በማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ወጣኝነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት መቋቋሙን አስታውቀዋል።
ዕቅዱ ከሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተደጋግፎ ለአስር አመታት የሚተገበር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ለዕውቀት ማበልፀጊያ የሚሆነውን የዚህን ስራ ወጪ ሙሉ በሙሉ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር እንደሚሸፍንም ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉን የሚመራ ዳይሬክተር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሰየም ሲሆን÷ በማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር የሚመራ አጠቃላይ አመራር የሚሰጥ የዳይሬክተሮች ቦርድም ይዋቀራል ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ።
“የዚህ የትምህርት ክፍል መቋቋም የማዕድን ዘርፉ በምናስበውና ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ዘመናዊነትን እንዲላበስ ለሚደረገው ጥረት እንደ ወሳኝ እርምጃ ይቆጠራልም” ብለዋል ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.