Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ፎረም በኳታር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ፎረም በትናንትናው ዕለት በኳታር ዶሃ ተካሂዷል።

በፎረሙ በኳታር የሚገኙ ኢንቨስተሮች፣ የተለያዩ የኩባንያ ባለቤቶችና ሃላፊዎች፣ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

እንዲሁም  በኳታር  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ አምባሳደር አብዱራህማን አልዶሶሪን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት ተወካዮች  ተሳትፈዋል።

በኳታር የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ በኳታር እና በኢትዮጵያ መካካል ያለው ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት እና የንግድ መናኸሪያ ከሆኑት ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የገለጹት አምባሳደሯ ፥ሀገሪቱ  ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማካሄድ ላይ የምትገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከበርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ጀምሮ ለውጭ ኢንቨስተሮች አስፈላጊውን የተሟላ የመሰረተ-ልማት አገልግሎት የምታቀርብ ሀገር መሆኗንም አውስተዋል።

በመድረኩ ላይ በግብርና፣ ሆቴል፣ ቱሪዝም ፣ በመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች ማምረት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ እና በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ የኳታር ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መኖራቸው ተገልጿል።

ፎረሙ በግብርና ማቀነባበሪያ ፣  በማምረቻው ዘርፍ፣ በሃይል ማመንጨት፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽንና ፋይናንስ ዘርፍ የተከፈቱ አዳዲስ እድሎች እንዲተዋወቁና ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚስችል መሆኑ ተመላክቷል።

ስለሆነም የኳታር  ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዘርፎች እንዲሰማሩ አምባሳደር ሳሚያ  ጥሪ ማቅረባቸውን በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሀገራቱን የኢንቨስትመንትና ንግድ እንዲሁም የባህል ትስስር ለማጠናከር የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ በመገባት ላይ መሆኑን ያብራሩት አምባሳደር ሳሚያ፥ ከእነዚህ መካከልም የኢንቨስትመንት ማስፋፊያና ጥበቃ ስምምት እና የንግድ ስምምነትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም በሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.