Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ወልዲያን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ወልዲያን ጨምሮ ሀራ፣ ሳንቃ፣ ስሪንቃ፣ ጎብዬ፣ ሮቢት እና ቆቦ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመራ የሚገኘው ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ማጥቃት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አከርካሪው በመመታቱ የጠላት ፍላጎት፣ የማድረግ ዐቅም እና ሥነ ልቦናው ብትንትኑ መውጣቱን አስታውቀዋል፡፡
የወገን ጦር፣ በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉትን ከፍተኛ ቦታዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ በዞብል ደቡባዊ አቅጣጫ ደግሞ የጉራ ወርቄ ከፍተኛ ሰንሰለታማ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ አጽድቶ፣ ቀደም ብሎ የተቆረጠውን የወልድያ መቀሌ መሥመር በማስፋፋት፣ ወደ ወልድያ በቅርብ ርቀት እየገሠገሠ መሆኑ ትናንት ማምሻውን መገለጹን አስታውሰዋል።
በዚሁ መሠረት ሌሊቱን በሙሉና ዛሬ ረፋዱን ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና የአፋር የጸጥታ ኃይሎች ከንሥሮቹ የአየር ኃይል ጋር ባደረጉት የተቀናጀ የማጥቃት ዘመቻ የሳንቃን፣ የሲሪንቃን፣ የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልድያ ከተማን፣ ሐራን፣ ጎብየን፣ ሮቢትን እና ቆቦን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ አስታውቀዋል፡፡
የወገን ጦር በእነዚህ አካባቢዎች የመጨረሻ ሙከራውን ሲያደርግ የነበረውን የጠላት ጦር መደምሰሱንም ተናግረዋል፡፡
ከድምሰሳ ተርፎ ወደ ጨርጨርና አላማጣ እየፈረጠጠ ያለውን ኃይል ደግሞ የወገን ጦር እግር በእግር እየተከታተለ ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ እያደረገው ይገኛል፡፡
የአካባቢው ኅብረተሰብ በተለይም ወጣቶች ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት በየጢሻው እየተሹለከለከ ለማምለጥ የሞከረውን የጠላት ጀሌ በመልቀም፣ ምንም ዓይነት ንብረት እና ተተኳሽ ይዞ እንዳይወጣ የላቀ የጀግንነት ጀብድ መሥራታቸውንም ዶክተር ለገሰ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ከተሞች ረዘም ላለ ጊዜ በጠላት እጅ የቆዩና አያሌ በደሎች ሲፈጸምባቸው የነበሩ በመሆናቸው፣ ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራና የአፋር የጸጥታ ኃይሎች ከንሥሮቹ የአየር ኃይል ጋር በመጣመር በፈጸሙት አስደናቂ የጀግንነት ገድል ነጻ በመውጣታቸው እንኳን ደስ ያላችሁም ነው ያሉት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በላሊበላና በሙጃ መካከል ሾልኮ ገብቶ ጋሸናን ለመቁረጥ ሲሞክር የነበረው የጠላት ኃይል በጀግናው የወገን ጦር ከበባ ውስጥ እንዲገባና እንዲደመሰስ በማድረግ የኀሙሲት፣ እስታይሽ፣ አሁን ተገኝ፣ ድልብ፣ ኩል መስክ እና አካባቢያቸው ሙሉ በሙሉ ከጠላት ነጻ መውጣታቸውንም አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ጀግናው የወገን ጦር የላሊበላ አካባቢን ከጠላት በማጽዳት፣ በሰቆጣ ከተማና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የመሸገውን የጠላት ኃይል እየደመሰሰ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም እግሬ አውጭኝ ብሎ ወደ ኮረም አቅጣጫ እየፈረጠጠ ያለውን ጠላት እግር በእግር እየተከተለ ሙት፣ ቀስለኛና ምርኮኛ በማድረግ ላይ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.