Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በአገሪቷ ላይ የተከፈተውን ያልተገባ ጫና ለመመከት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአገሪቷ ላይ የተከፈተውን ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመመከት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ።

መንግስት በትግራይ ክልል ከወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ ምክንያታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን  በኢትዮጵያ ላይ  ለመፍጠረ  እየሰሩ ያሉ  አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን መኖራቸው ይታወቃል።

በዚህም የኢትዮጵያን መልካም ስም በሚያጎድፍና በሚያጠለሽ መልኩ ሀሰተኛ መረጃ ሲነዛ ቆይቷል ብሏል ኤጀንሲው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደተናገሩት÷ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ይህንኑ ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመቀልበስ ጥረት እያደረገ ነው።

መንግስት በትግራይ ክልል የትኛውም ቡድን የከፋ ጉዳት እንዳይገጥመው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሠብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ትክክለኛ መረጃ ለዓለም እያደረሱ አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም ኤጀንሲው ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲይዝ ዳያስፖራውን የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰላማዊት ገለጻ ኤጀንሲው ይህን ተገቢ ያልሆነ ጫና ለመቀልበስ በተለያዩ ዓለምዓቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር እየሰራ ነው።

በተጨማሪም የሚዲያ ባለቤቶችና ለሚዲያ ቅርብ የሆኑ ሰዎች፣ የዳያስፖራ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ክልልን የተመለከቱ ሀሰተኛ መረጃዎችን እንዲመክቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት በአሜሪካ፣ በካናዳና በጄኔቫ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሠላማዊ ሠልፍ በማካሄድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል።

የሠላማዊ ሠልፎቹ መልዕክት በዋናነት ማንም ሶስተኛ ወገን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል ያመላከተ እንደሆነም አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ የዳያስፖራው ማሕበረሰብ ሠልፍ ከማድረግ ባለፈ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለምዓቀፍ ተቋማትና ለመንግስታት እውነታውን እንዲረዱ ፊርማ አሰባስበው መላካቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዝኛና በዓረብኛ ቋንቋዎች ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚያንፀባርቁ ጽሁፎችን እየጻፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የዳያስፖራው ማሕበረሰብ በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የሶስተኛ ወገን ጫና ለመመከት መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.