Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ወራት ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

የድርጅቱን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ ሃና አርአያስላሴ መግለጫ ሰጥተዋል።

ወይዘሮ ሃና እንዳሉት፣ ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ሚሊየን በላይ የፖስታ ትራፊክ ያንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከ90 በመቶ በላይ እቅዱን በማሳካት 233 ሚሊየን ብር ገቢ አግኝቷል።

ገቢው የተገኘው ከደብዳቤ፣ ጥቅልና ኢ.ኤም. ኤስ አገልግሎቶች ሲሆን፤ የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የቤት ለቤት የፖስታ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም የተገኘበት ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ድርጅቱ ገጥሞት በነበረው ብልሹ አሰራር ሳቢያ የበጀት መዝጊያው ላይ 34 ሚሊየን ብር ኪሳራ ገጥሞት እንደነበረ አስታውሰው አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል።

ከእርምጃዎቹ ውስጥ ቁጥጥሩ የጠበቀ ማድረግ አንዱ መሆኑን ያብራሩት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የፋይናንስ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ከየቅርጫፎቹ የሚሰበሰበው ገቢ ወደ ማዕከል ፈሰስ እንዲደረግ ማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ድርጅቱ እስከ 10 ዓመት ድረስ የቆየ እዳዎች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የግብር እዳ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን ገልጸው፤ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል ዓለም አቀፉ የሂሳብ አያያዝ አይ.ኤፍ. አር.ኤስ አሰራርን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎትም ፈጣን ለማድረግ ተገቢውን የሰው ኃይል ያሟላ ዲፓርትመንት እንዲቋቋም የተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የደንበኞች ቅሬታ አፈታትና ካሳ ክፍያ ላይም ያለውን ችግር የማስተካከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የመልዕክት ደህንነት ላይ ከበፊቱ የተሻለ ነገር ቢኖርም የሚጠበቀው ያህል አይደለም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከመልዕክት መጥፋት ጋር በተያያዘ ድርጅቱ 200 ሺህ ብር ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታውቀዋል።

ድርጅቱ ገቢውን ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችም የጀመረ ሲሆን፤ ጡረታና ክፍያ፣ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች የውክልና ክፍያ በመፈጸም ገቢ እየሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ ቪዛ አመልካቾችን ፓስፖርት የማድረስ ስራ መጀመሩን ገልጸው፤ አገልግሎቱን በአዲስ አበባ፣በባህዳርና በሀዋሳ ለሚገኙ ደንበኞች እየሰጠ ነው ብለዋል።

ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 900 ቅርጫፎች ያሉት መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.