Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ሱዳን አጎራባች አካባቢዎችን ሠላም ለማረጋገጥ እና የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ሱዳንን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሃንስ ከተማ አስተዳደር ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን እና የሱዳን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ውይይት ተካሄደ።

የውይይቱ አጀንዳ የሁለቱ አጎራባች ሀገራት ድንበር ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በግብይት እንቅስቃሴ ወቅት በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ደሳለኝ ጣሰው ÷ የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበት የሚያመላክቱ የመወያያ ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረገውን ግንኝነት በማጠናከርም ግንኙነቶቹን ከድንበር ከተሞች በዘለለ እስከ አዲስ አበባና ካርቱም ድረስ ለማዝለቅ ፍላጎት እንዳላቸው የሱዳኑ የጦር መሪ ብርጋድየር ጀነራል በሽር ሰኢድ ገልፀዋል።

በሁለቱም ህዝቦች መካከል ከመፋቀርና በጋራ ተባብሮ ከመኖር ውጭ ምንም ዓይነት ቅራኔ እንደሌለም አብራርተዋል።

የሱዳን መንግስት ከፍተኛ አመራርም በሰጡት አስተያየት ሁለቱም ህዝቦች ከምንም በላይ የሚዋደዱና የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርም ውይይቱ መልካም ጅማሮ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

በሱዳን ቀጠናዎች ዙሪያ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት፣ የጉምዝ እና የቅማንት ፅንፈኛ ኃይሎች እንዲሁም የሸኔ አሸባሪዎች እንደሚገኙ የተመለከተ ሲሆን፥ እነዚህ ኃይሎች በሱዳን በመመሸግና መነሻቸውን በማድረግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ችግር ሲያደርሱ እንደነበር አስታውሰው በጋራ ለመፍታት መነጋገር እና መግባባት ላይ ሊደረስ ይገባል ብለዋል።

በድንበር የሚገኙ የሁለቱንም ህዝቦች የጋራ ጠላቶች በመተባበር ማስወገድ ይኖርብናልም ነው ያሉት አመራሮቹ በውይይታቸው።

የሱዳን ጉምሩክ ኃላፊ አህመድ ሰኢድ በበኩላቸው÷ ከባድ የጭነት ማጓጓዣዎች ገብተው የንግድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ግንኙነቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

የሱዳንና የኢትዮጲያ መከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ፖሊስ እና ሚሊሺያዎች ቀጣናውን በተጠናከረ መልኩ ለመጠበቅና ሠላምን ለማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደሚሰሩም ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የምዕራብ ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላከተው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.