Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚቻለው ሀገራቱ ባቋቋሟቸው መዋቅሮች ብቻ ነው-አቶ ውሂብ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚቻለው ሁለቱ ሀገሮች ባቋቋሟቸው መዋቅሮች ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አቶ ውሂብ ሙሉነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን አባል አቶ ውሂብ ሙሉነህ ለኢዜአ እንደገለጹት የሁለቱ ሀገሮች የድንበር ማካለል ጉዳይ ለ118 ዓመታት የዘለቀ ነው።

በፈረንጆቹ 1902 ጉዊን የተባለ እንግሊዛዊ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የማካለል ስራ መስራቱንና የማካለሉን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርት ማቅረቡን አስታውሰዋል።

ይሁንና ጉዊን የድንበር ማካለሉን ያደረገው ያለ ኢትዮጵያ መንግስት እውቅና በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርቱን ውድቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በፈረንጆቹ 1972 የሀሳብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ድንበራቸውን እንደገና ለማካለል መስማማታቸውን ነው አቶ ውሂብ ያስረዱት።

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ሀገራት የሚቀበሉት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የድንበር ነባራዊ ሁኔታው ባለበት ተከብሮ እንዲቆይ መስማማታቸውን አመልክተዋል።

በፈረንጆቹ በ2002 ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ ድንበር ቴክኒክ ኮሚቴ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴ አቋቁመው ለድንበሩ ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት ሲሰሩ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የድንበር ኮሚሽኑ በኮሚቴዎቹ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን በመገምገም ለአገራቱ መንግስታት ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የጋራ የድንበር ቴክኒክ ኮሚቴው በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ቅኝት ማድረጉም ይታወሳል።

የጋራ ልዩ ኮሚቴው በሀሳብ ልውውጥ ስምምነቱ አማካኝነት የመፍትሔ ሀሳብ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችሉ ስብሰባዎችን አድርጎ የመጨረሻ ሪፖርት ባላቀረበበት ሁኔታ ሱዳን ሃይል ተጠቅማ የኢትዮጵያ መሬት መያዟን ነው አቶ ውሂብ የገለጹት።

ሱዳን ይህንን ማድረጓ እ.አ.አ በ1972 የሀሳብ ልውውጥ መሰረት አማካኝነት ነባራዊ ሁኔታውን የማስቀጠል ስምምነት መጣሷንና ለፈረመችው ስምምነት ተገዢ አለመሆኗን ተናግረዋል።

ሱዳን ያስመለስኩት መሬቴን ነው በሚል የምታቀርበው ሀሳብም ስምምነቱን ያላከበረ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን ለመፍታት ያቋቋሟቸውን የጋራ መዋቅሮች ተጠቅመው መፍትሔ ማበጀት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.