Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ስዊድን የሁለትዮሽ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና በስዊድን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ራይድበርግ የተመራ የኢትዮ ስዊድን የሁለትዮሽ ምክክር ተካሄደ፡፡

በውይይቱ በሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነቶችና የልማት ትብብር እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ ከሱዳን ጋር የተፈጠረው የድንበር ችግር፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሁም ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበርን ማካለል እንዲቻል ሃገራቱ የጋራ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተው፥ ሱዳን በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በወረራ መያዟን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት ያላት መሆኑን እንዲሁም በሱዳን በኩል የታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የምታነሳቸው ጥያቄዎች መመለሳቸውንና የምታራምደው አቋም ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረር መሆኑን አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ በአብዛኛው በመንግስት እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው፥ “በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል ግን ምንም እንኳ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለማድረግ ሲጠየቁ የነበሩ ምቹ ሁኔታዎች የተመቻቹ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ተጨባጭ አስተዋጽኦ አልተደረገም” ብለዋል።

ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫን በተመለከተም ነጻ እናገለልተኛ ሆኖ እንዲካሄድ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም መደረጉ አንስተዋል።

የስዊድን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ራይድበርግ በበኩላቸው፥ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ረጅም ዘምን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው በልማት ትብብሮች ዘርፍ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከኢትየጵያ እንደተጀመረ አስታውሰዋል።

ስዊድን የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እያከናወናቸው ያሉና የተሻሻሉ ተግባራትን እውቅና እንደምትሰጥ፣ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንደሚያስፈልግ፣ የድንበር ውዝግብና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ መንግስታቸው እንደሚያበረታታ እንዲሁም መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ስዊድን አሳታፊና ተአማኒ ምርጫ እንደምትጠብቅ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በተያያዘም ስዊድን ለኢትዮጵያ የሪፎርም ፕሮግራሞች ተቋማዊ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ጠቅሰው፣ የሁለቱን ሃገራት የልማት ትብብር ለማስቀጠል ስዊድን በፈረንጆቹ ከ2022 እስከ 2026 የሚያገለግል ሃገራዊ ፕሮግራም እያዘጋጀች ትገኛለች ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.