Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በሻንጋይ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በሻንጋይ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት በጋራ በሻንጋይ ከተማ ተከበረ።

በበዓሉ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ በበይነ መረብ ተሳትፎ በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ በሻንጋይ  ቆንስላ ጄኔራል አቶ ወርቃለማሁ ደስታ እና የቻይና የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ወይዘሮ ጽዮን ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ እና ግንኙነቱ ሁሉን አቀፍ መሆኑንም አንስተዋል።

ሁለቱ ሃገራት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስም በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳትፎ የቻይና ባለሀብቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዙ አንስተዋል።

አያይዘውም ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የሚያደርጉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበኩላቸው በቻይና የሚገኙ ሚሲዮኖች በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች ታሪካዊ በዓሉን እያከበሩ እንደሚገኙ ገልፀው፣ በቀጣዩ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ቻይና አጋርነቷን አጠናክራ እንድምትቀጥል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በዓመቱ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የቻይና መንግስት እና የቢዝነስ ማህበረሰብ ለታዳጊ ሃገራት በተለይም ለኢትዮጵያ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የቻይና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶች፣ የንግድ ማህበረሰብ፣ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እና የዳያስፖራ አባላት እንዲሁም፤ በሻንጋይ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.