Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-አውሮፓ ሕብርት የጋራ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የጋራ ምክክር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ ደመቀ መኮንን እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም በጋራ በመመራት ተካሂዷል።

ምክክሩ በኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የትብብር ጉዳዮች፣ የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ እንዲሁም በቀጣይ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ በማተኮር የተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል።

በወቅቱም አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል የሚደረገው ቋሚ ምክክር በኮቶኖ ስምምነት እንዲሁም በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካልል እ.ኤአ በ2016 የተፈረመውን የስትራቴጂያዊ የትብብር ሰነድን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ተሳታፊ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮችም በሰጡት አስተያየት÷ ህብረቱ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት በተያዩ መልኩ ድጋፍ ማደረጉን አስታውሰው÷ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርስባትን ተጽዕኖ ለመከላከል የተከተለችውን መንገድ እንደሚያደንቁ ጠቅሰዋል።

የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ቅንጅታዊ አሰራሮች የበለጠ ለማሻሻል የሚቻልባቸው መንገዶች እንዲታዩ፣ በክልሉ የግብርና ተግባራት ትኩረት የሚሹ ስለመሆኑ፣ መንግስት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረትን የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም  በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ተቋም መካከል ገለልተኛ የጋራ ምርምራ ለማድረግ የተጀመረው ሂደት እንደሚያደንቁ  ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ስደተኞች ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እንዲሁም መንግስት ለፕሬስ ነጻነት ተገቢው ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም መደረጉን እንደሚያደንቁ ገልጸው፣  ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ከሎጀስቲክ ስርጭት አንጻር የሚያጋጥሙ ችግሮች ትኩረት መሰጠት ያለበት መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው÷ ምንም አንኳ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች የተከሰቱ ቢሆንም እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የደቀነው አሉታዊ ተጽእኖ ቢኖርም ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በመፍጠሯ የውጭ ቀጥታ አንቨስትመንት ፍሰት ከመሳብ አንጻር አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን አንስተዋል።

አያይዘውም ህጎች ለኢንቨስተሮች ምቹ  ሁኔታን ለመፍጠር ዓላማ በማድረግ እንደሚወጡ  ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ኢንቨስተሮች የሚያጋጥማቸውን ማነቆዎች ለመፍትታ አገራዊ የቅንጅት መድረክ መቋቋሙን አንስተው÷ የአውሮፓ ህብረት አገራት ኩባንያዎችም የሚጋጥማቸውን ተግዳሮቶች በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ለመከላከል ከአውሮፓ ህብረት ለተደረገው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተም በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ለሚሰማሩ አካላት ያልተገደበ ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን አስታውሰው÷ ለእርዳታ አቅራቢ ሰራተኞች ደህንነት ሲባል በተወሰኑ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

ነግር ግን  በአጠቃላይ በክልሉ የተደራሽነት ችግር መኖሩን አመላካች አለመሆኑን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊዎችን በተመለከተ የሚቀርበው አሀዝ ቀደም ሲል በክልሉ ያሉና የተለየ ሀብት የተመደበላቸውን ተፈናቃዮች፣ የምግብ ዋስትና ተረጂዎች እንዲሁም ስደኞችን ቁጥርን ከግምት ያላስገባና የተጋነነ መሆኑን አንስተዋል።

አክለውም በሲቪል እና ወታደራዊ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽ ለማሳደግ የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ የግብርና ስራዎች የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ የግብርና ግብዓቶች የማቅረብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እየወጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሂደቱን ለማፋጠን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በትግራይም የተፈናቀሉ ዜጎች ከዝናብ ወቅት በፊት ለመመለስ እንዲቻል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ስራዎች እየተከናወኑ ስለሆኑም ገልጸዋል።

የሕወሓት ቅሪቶች በክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር አባላት እና ሌሎች ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ ማድረግ መቀጠላቸውን ጠቅሰው÷ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁኔታውን በሚዛን በማየት መሰል ተግባራትን በይፋ መኮንን እንደሚገባው ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ወደ ሌላ በማዛወር አስፈላጊው ግብዓት በሟሟላት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን እንዲሁም ተጨማሪ መጠለያዎችን የማቋቋም ስራዎች ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሸን ጋር በመተባበር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ የፌደራል ፖሊስ ከሚሽን ከትግራይ ክልል ጊዚዊ አስተዳደር ጋር በመተባበር አስፈላጊው ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

የፕሬስ ነጻነትን በተመለከተም መንግስት ከመቸውም ጊዜ በላይ የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ማድረጉን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ባፈነገጠ መልኩ የተለየ ተልዕኮ በመያዝ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ጋዜጠኞች ስለመኖራቸው አንስተዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከናወን መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉንመግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.