Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ካናዳ የጋራ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮ-ካናዳ የጋራ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ
ፎረሙ በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማሳደግ አላማ ያደረገ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷  ሁለቱ ሀገራት ከ1948 ዓም ጀምሮ ጠንካራና ሁሉን አቀፍ የሆነ የሁለትዮሽ ትብብሮች መመስረት እንደቻሉ ገልፀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ትብብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ይፋዊ ጉብኝቶች መደረጋቸውን አምባሳደር ማህሌት ጠቁመዋል።

በሁለቱ ሀገራት መንግስታት መካከል ከተደረገው  ግንኙነት በተጨማሪ የቢዚነስ ትስስር መፍጠር መቻሉ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዳሸጋገረው በመግለፅ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል አቅም እንዳለ ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት 10 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙት አምስት ታላላቅ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዷ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ማህሌት ገልጸዋል።

አዲሱ አመራር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያሉበትን ችግሮች መዋቅራዊ በሆነ መልኩ በመፍታት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር በቁርጠኛነት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የካናዳ ባለሀብቶችም በተለያዩ የማምረቻ ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ አምባሳደር ማህሌት ጥሪ አቅርበዋል።

የካናዳ የውጭ ንግድ ስምምነቶች ማስፋፊያ ዳይሬክተር ሚስ ሲንዳይ ኢቭ ቦራሳ በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.