Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ- ኬንያ የድንበር ጉዳይ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ በናይሮቢ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ኬንያ የድንበር ጉዳይ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ተጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ የቴክኒክ ቡድን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድንበሮች አማካሪ በውሂብ ሙሉነህ የተመራ ሲሆን፥ በኬንያ በኩል የአገሪቱ አለም አቀፍ ድንበሮች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ጆን ሙጌንዲ ተመርቷል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም፥ ሁለቱ እህትማማች ሀገራት መልካም የሆነ እና ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ገለጽው ፥ ግንኙነታቸው በመከባበር እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ነውም ብለዋል።

ግንኙነቱ የሚገለጸው በሁለቱ አገራት መሪዎች ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና በህዝቦቻችን መካከል በተለይም በጋራ ድንበር አካባቢ ያለው ግንኙነት ጠንካራ በመሆኑ ነው ሲሉ አምባሳደር መለስ አብራርተዋል።

አምባሳደሩ የዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ምክክር በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተውን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጎለብት እንደሆነ ገልጸው ፥ ይህም በተለያዩ የጋራ ድንበር ጉዳዮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባዎች ሲረጋገጥ መቆቱንም ነው ያነሱት።

የሁለቱን አገራት የድንበር ላይ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሁለቱም ወገኖች አስፈላጊውን የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የሎጂስቲክስ ግብዓት በመመደብ እንዲሰሩም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በሚካሄደው የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ፥ በ “የሞምባሳ ሪፖርት” ተብሎ በሚታወቀውና በ2019 በተደረሰው ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያና በኬንያ አዋሳኝ አካባቢዎች በቁጥጥርና ጥገና ሥራ፣ በደህንነትና ሰላም ማረጋገጥ ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ፥ የበጀትና የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ዙሪያ ኬንያ እና ታንዛኒያ የድንበር እንቅስቃሴን አስመልክቶ ባላቸው ተሞክሮ ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል የድንበር ስምምነት ተደረገው በ1970 ዓ.ም. እንደሆነ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.