Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ ለመስራት በሚስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተፈራረሙ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር በባቡር መስመሩ ላይ የሚታየውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቅርፍ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አስኪያጅ አቶ አሸብር ባልቻ ናቸው የተፈራረሙት፡፡

በሁለቱ ተቋማት የተደረገው ስምምነት ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ እና በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሲሆን÷ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በአጭር ፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ጉዳዮች መለየታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ÷ ስምምነቱ በባቡር መስመሩ ላይ የሚታየውን የኃይል መቆራረጥ ችግር የሚያስቀር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አስኪያጅ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው÷ ተቋማቱ ያላቸውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እና ያላቸውን ሀብት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ተቋማት ተቀናጅቶ መስራት ለተቋማቱም ሆነ ለሀገርቱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም ተመላክቷ፡፡

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.