Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 400 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዷል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2013 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 400 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ለ45 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማሰቡንም የኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ደበሌ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው በ2017 የዓለም ምርጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚና አስተዳዳሪ የመሆን ራዕይ አንግቦ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ዘርፉን የሚመጥን ዕቅድ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው÷ በበጀት ዓመቱ 36 የሀገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኮች ለማስገባት እየሰተሰራ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የተገነቡ ፓርኮችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ በማስገባት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ ባለፈ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራልም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በተያዘው በጀት ዓመት የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ለልማት ዝግጁ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ጥረት ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ለአንድ ወገን የሚተው እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ደርቤ፣ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ የኃይል መቆራረጥ፣ የውሃ አቅርቦት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አካላት ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት 31 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ለፓርኮቹ ሠራተኞች እንደሚገነቡ የገለጹት ኃላፊው፣ በቦሌ ለሚ-1 ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ባለሃብት የመኖሪያ ቤት ግንባታ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ኃላፊው የሀገር ውስጥ አምራች ኢንተርፕራዞችን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ገበያ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እንደ ሀገር ባለሃብቶች የሥራ ደህንነት ተሰምቷቸው መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አቶ ደርቤ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 165 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ ውጭ ልኳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.