Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን  ፓርኮች ለሰራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤት እንዲያቀርቡ እያግባባ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሰራተኞቻቸው  የመኖሪያ ቤት ገንብተው እንዲያቀርቡ እያግባባ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን  አስታወቀ።

ሰራተኞች በኢንዱስትር ፓርኮች ተረጋግተው እንዳይሰሩ  የቤት ችግር ዋነኛው እንቅፋት ሆኖ እየተስተዋለ ነው።

ፓርኮቹ የሚገኙባቸው ከተሞችም ችግሩን ለመፍታት ሀላፊነት ቢኖርባቸውም ለመፍትሄ ሲሰሩ ግን አይታይም።

ሁኔታው እንዳሳሰበው የሚገልፀው  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በፓርኮቹ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ሌሎች ባለሃብቶች ለሰራተኞች ቤት ገንብተው እንዲያቀርቡ እያግባባ መሆኑን ነው የገለፀው።

ለሰራተኞቹ  ቤት ገንብቶ በማቅረብ የሚለቁ ሰራተኞችን በአንድ ወር ከ85 በመቶ በላይ መቀነስ የቻለውን በቦሌ ለሚ የሚገኝ የደቡብ ኮሪያው ሺንቲስ ድርጅትን እንደማሳያ በመጠቀም በተጀመረው ጥረት ውጤት እየታየ መሆኑንም ነው የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሌሊሴ ነሚ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ዋና ስራ አስፋጸሚዋ በፓርኮች ውስጥ የማይሰሩ ነገር ግን ፍላጎት ያላቸው የግል ድርጅቶችም ቤቶችን ገንብተው እንዲያቀርቡ የማስተዋወቅ ስራ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ሌሎች ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሰራተኞች ጥያቄዎችን በተመለከተ ደግሞ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገሪቱን የዝቅተኛ ክፍያን ለመወሰን እያደራጀ ባለው ተቋም እና እየተዘጋጀ ባለው ህግ የሚመለስ ይሆናል ብለዋል።

በሀገሪቱ ካሉ አስራ ሁለቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሰባቱ ወደ ስራ የገቡ ናቸው።

እነዚህም ፓርኮች ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል።

 

በትግስት አብርሃም

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.