Fana: At a Speed of Life!

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሙስና ጥቆማና ሃብት ምዝገባ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለሙስና ጥቆማና ሃብት ምዝገባ አገልግሎት ያበለጸገውን መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

በዓለም ለ17ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የጸረ-ሙስና ቀንን ኤጀንሲው ዛሬ አክብሯል።

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ሙስናን ለመከላከል አጋዥ የሆነ መተግበሪያ ማበልጸግ እንደተቻለ አብራርተዋል።

አዲሱ መተግበሪያ ጥቆማ መቀበል፣ የሃብት ምዝገባና ሪፖርት ማሳየት ከሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከሙስና ጋር ተያያዥነት ያላቸው መረጃዎችን ማሳወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በእጅ ስልኩ ወይም በኮምፒውተር በኢንተርኔት ታግዞ ካለበት ቦታ ጥቆማ መስጠት እንዲችል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

መተግበሪያው ለኤጀንሲው ሰራተኞች ሃብታቸውን ያስመዘገቡ፣ ያላስመዘገቡና ጊዜ ያለፈበትን መረጃ በቀላሉ ለመቆጣጠርና ለመከታተል ያስችላቸዋል ተብሏል።

አሰራሩ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ጥቆማ በመስጠት መረጃ የሚሰጠውን አካል ደህንነት በመጠበቅና ለትክክለኛው አካል እንዲደርስ በማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለውም ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

አሰራሩን ከስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በማቀናጀት ሃብታቸውን ያስመዘገቡና ያላስመዘገቡትን የኤጀንሲው ሰራተኞችና አመራሮች በቀላሉ ማወቅ ያስችላል።

ሌሎች መንግስታዊ ተቋማትም መተግበሪያውን በነጻ በመውሰድ የሰራተኞችን የሃብት መረጃ  በአንድ ቋት ማደራጀት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ፤ “ኤጀንሲው ያበለጸገውን ሶፍትዌር ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት እንዲጠቀሙበት ይደረጋል” ብለዋል።

አሰራሩ የጸረ-ሙስና ትግልን በዘመናዊ መንገድ ከመከታተል አኳያ ያለው አስተዋፆዖም ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ኮሚሽኑ የመንግስት ተሿሚዎችንና ሰራተኞችን ሃብት ከወረቀት ነጻ አድርጎ ለማደራጀት እያበለጸገ ያለው ዘመናዊ አሰራር እየተጠናቀቀ መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።

በዛሬው መርሃ ግብር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከፍተኛ አመራሮችና ተሿሚዎች ሃብታቸውን ማስመዝገባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.