Fana: At a Speed of Life!

የኢድ አልፈጥር በዓል በአማራ ክልል በባህር ዳር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሀን ከተሞች ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 443ኛዉ የኢድ አልፈጥር በዓል በባህር ዳር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሀን ከተሞች ተከበረ፡፡

በዓሉ በባህርዳር ሲከበር ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሀመድ የእስልምና እምነት ተቋማትንና የእምነቱን ተከታዮች የሚያነጣጥሩ ጥቃቶች ሊቆሙ ይገባል፤ መንግስትም የድርጊቱ ፈፃሚዎቾ ለህግ እንዲቀርቡ ይስራ ሲሉ ጠይቀዋል።

በሌሎች የእምነት ተቋማትና ተከታዮቻቸውም ላይ የሚፈፀምን ድርጊት እንደሚያወግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ በዓሉ በደሴ ከተማ በፉርቃን መስጅድ ተከብሯል።

በአከባበሩ የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እና የደሴ ከተማ ህዝባዊ መጅሊስ ሊቀመንበር ሸህ እንድሪስ በሽርን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት አመራሮችና የሀይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በተመሳሳይ በደብረብርሃን ከተማ በዓሉ የተከበረ ሲሆን፥ በበዓሉ ላይም የሰሜን ሸዋ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ ዜይን “የሀገራችንን ሰላምና ወንድማማችነት መንፈስ በጋራ ልንጠብቅ ይገባል” ብለዋል፡፡

“እርስ በርስ ሊያጣሉን የሚፈልጉ የጥፋት ሃይሎችን በጋራ እናወግዛለን፤ መንግስትም አጥፊዎችን በህግ ሊጠይቅ ይገባል” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፥ ኢትዮጵያውያን ዕምነት ሳይገድባቸው በመከባበርና በመዋደድ በጋራ የመኖር የቆየ ዕሴት ያላቸው ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡

ይህንንም በዓል ከተቸገሩ ከተፈናቃይ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ማክበር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በፀጋየ ወንደሰን፣ ዘላለም ገበየሁ እና አንድነት ናሁሰናይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.