Fana: At a Speed of Life!

የኢድ አል አድሀ በዓል በመላው ሀገሪቱ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አድሀ/አረፋ በዓል በመላው ሀገሪቱ ተከበረ።

በዓሉን በማስመልከትም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመተዛዘንና ያለውን በማካፈል የአረፋ በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር ነው ያሳሰቡት፡፡

በመግለጫቸውም ህዝበ ሙስሊሙ ይህን አስቸጋሪ ወቅት በመተዛዘንና ያለውን በማካፈል በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብር ጠይቀዋል።

የአረፋን በዓል ልዩ የሚያደርገው ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት፣ መተዛዘንን፣ አብሮነትንና መረዳዳትን የምናሳይበት የእርድ ስነ ስርአት የሚከወንበት በዓል በመሆኑ ነው ብለዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በርካታ ወገኖች ለችግር የተጋለጡበት ወቅት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ተካፍሎ በመብላት በአሉን ማክበር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ከሚከናወነው እርድም አንድ ሦስተኛው ለምስኪኖች መስጠት ይገባልም ነው ያሉት።

የዘንድሮው የአረፋ በዓል እንዳለፈው ኢድ በመራራቅና ራስን ከኮሮና ወረርሽኝ በጠበቀ መልኩ መከበር እንዳለበትም ማሳሰባቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዘንድሮ አረፋ በዓል ሀገራችን ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ውሃ ሙሌት ያከናወነችበት ወቅት በመሆኑም ተጨማሪ ደስታ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ልማት ለማስቀጠልም ሰላም ዋነኛው በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ለሰላም ዘብ በመቆምና በመፀለይ በይቅርታ ወደ ፈጣሪው መመለስ ግድ የሆነበት ወቅት ላይ መደረሱንም አብራርተዋል፡፡

የአረፋ በዓል አደምና ሐዋ የተገናኙበት ሥፍራ እንደሆነ የጠቆሙት ሐጅ ዑመር እድሪስ የአረፋ በዓል ከነብዩላህ ኢብራሂምና ከእስማኤል ጀምሮ ሲከበር የነበረ በዓል መሆኑንም አብራርተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.