Fana: At a Speed of Life!

የኤሊዳአር በልሆ የመካከለኛ መስመር የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 29 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤሊዳአር በልሆ ወረዳ የመካከለኛ መስመር የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ተጠናቆ ተመረቀ፡፡
ኢትዮጵያ በጅቡቲ ድንበር ከምትጠቀምባቸው ወደቦች አንዱ የሆነው የታጁራ ወደብ ምስረታ ጋር ተያይዞ የተዘረጋው 27 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የመካከለኛ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ አገልግሎት ላይ መዋሉ ለጉምሩክና ኢሚግሬሽን አገልግሎት የላቀ ጥቅም ይሰጣል ሲሉ የጋላፊ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱ አሊ ገልፀዋል፡፡
አቶ አብዱ አሊ ከዚህ በፊት በጄኔሬተር ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው÷ ስራዎችን በተያዘለት ጊዜና በተገቢው መንገድ ለማከናወን ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም ይህ ፕሮጀክት መጠናቀቁ ስራዎቻቸውን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን እንደሚረዳቸውም ነው የገለጹት፡፡
ከመሠረተ ልማት አውታሮች አንዱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መሆኑን የገለፁት የኤሊዳአር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የአቅም ግንባታ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብደላ ሱሌ÷ አገልግሎቱ በወረዳዋ የኢኮኖሚ መነቃቃት እና ለወጣቶችም የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን አሊ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ በተያዘለት በጀትና በሚፈለገው ጊዜ መጠናቀቁ ለስራው መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.