Fana: At a Speed of Life!

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ሃገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ሃገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል፡፡

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በመድረኩ እንደገለፁት ተቋሙ አስተማማኝ፣ ፍትሀዊና ተደራሽ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ለማስፈን ሰፊ የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው፡፡

ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና ሃገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ ‘የብርሀን ለሁሉ’ መርሀ-ግብር ተግባራዊ ተደርጎ እ.ኤ.አ በ2025 ዓ.ም 65 በመቶ የሚሆነው ህብረተሰብ ከብሄራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲሁም 35 በመቶው ደግሞ ከብሄራዊ ግሪድ ውጪ ወይም በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ የውስጥ አሰራሩን ለማዘመን የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ሲስተም፣ የዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ አዘገጃጀት፣ የራዲዮ ኮሙዩኒኬሽን ፕሮጀክቶችን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የድህረ ክፍያ ቆጣሪ ንባብ፣ የዲስትሪቢዩሽን ዲጂታይዜሽን፣ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ሲስተም አገልግሎት ማስፋፋትና ለደንበኞች የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ አንስተው፤ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የዲሰትሪቡሽን መልሶ ግንባታና አቅም የማሳደ ስራዎች መተግበራቸው አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና የውስጥ አሰራርን ለማዘመን ማገዙን አመላክተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የደንበኞች የመክፈል አቅም ታሳቢ ባደረገና ፍትሀዊነትን ባረጋገጠ መልኩ ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም በየዓመቱ ተከፋፍሎ ተግባራዊ የሚደረግ የታሪፍ ማስተካከያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ በያዝነው ወርም የማስተካከያው ሶስተኛው ዙር እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡

የፋይናንስ ዕጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የኢነርጂ ብክነትና ስርቆት፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆቶችና አደጋዎች፣ የዲስትሪትሪቡዩሽን ኔትዎርኩ በማርጀቱ ለኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እየሆነ መምጣቱ የተቋሙ ማነቆዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

መድረኩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በተቋሙ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ለመምከር የተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳ ችለናል፡፡

በውይይቱ ላይም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫላ ለሚ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈቲያ የሱፍ፣ ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት እና የተቋሙ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.