Fana: At a Speed of Life!

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
 
ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከትር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።
 
በተጨማሪም በአዳማ፣ ቢሺፍቱ እና ዱከም የሚገኙ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
 
ትናንት መሪዎቹ በጋራ በአዲስ አበባ አዲስ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃም የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
 
በዚህ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት ወቅት ሀገራቱ በርካታ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው ተመልክተናል፤ ይህንንም ለመጠቀም ተወያይተናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።
 
የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ከድህነት ለማስወጣት ያለ መታከት እንሰራለንም ነው ያሉት።
 
የፈረንጆቹ 2020 ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝቦች ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ የብልፅግና መጀመሪያ ዓመት ይሆናልም ብለዋል።
 
በኢትዮጵያ በኩል ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ብልፅግና አብሮ መስራት በኢትዮጵያ በኩል ሙሉ ዝግጁነት እንዳለም ጠቁመዋል።
 
የአሁኑ የሁለት ቀናት ጉብኝቴ የሁለት ወራት ቆይታን ያህል ነው የተሰማኝ ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ ጉብኝቱ በበርካታ በድንገቴ አስደሳች ሁነቶች የተሞሉ መሆኑን ነው የገለፁት።
 
ለልዑካቸው ለተደረገው አቀባበልም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምስጋና አቅርበዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንድአርጋቸውን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሸኛኘት አድርገዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.