Fana: At a Speed of Life!

የኤርትራ ስደተኞችን አገልግሎት ወደሚሰጡ የመጠለያ ጣቢያዎች ለመመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኤርትራ ስደተኞችን አገልግሎት ወደሚሰጡ የመጠለያ ጣቢያዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በትግራይ ክልል በሽመልባ የስደተኛ መጠለያ 8 ሺህ 400፣ በህጻጽ 11 ሺህ 800፣ በማይዓይኒና በአዲሀሩሽ የስደተኛ መጠለያዎች በድምሩ 29 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች ይኖሩ እንደነበር ገልጸዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው በጀመረበት ወቅት በኤርትራ ስደተኛ መጠለያዎች ይሰጥ የነበረው አገልግሎት መቋረጡን አስታውሰው፤ የጸጥታ ስጋት በነበረባቸው ሽመልባና ህጻጽ ካምፖች የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች ከመጠለያዎቹ በመውጣት ወደተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

የህጻጽ የስደተኞች መጠለያ በበረሃ የሚገኝና ለኑሮ አመቺ አለመሆኑንም አመልክተው፤ የስደተኞች መጠለያዎቹ መስፈርቱን ስለማያሟሉ በመንግስት ውሳኔ መዘጋታቸውንና የኤርትራ ስደተኞች በአዲ ሀሩሽና ማይ አይኒ መጠለያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም እስከ መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ከህጻጽና ሽመልባ መጠለያዎች የወጡ 7 ሺህ 16 ስደተኞች ወደ አዲ ሐሩሽና ማይ አይኒ እንዲመጡ መደረጉን ነው አቶ ተስፋሁን የገለጹት።

ከተዘጉት መጠለያዎች ሌሎች ኤርትራውያን ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች፣ አማራና አፋር ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ሄደዋልም ነው ያሉት።

ኤጀንሲው ባደረገው ማጣራት የኤርትራ ስደተኛ መሆናቸው የተረጋገጡ ዜጎች በያሉበት ሆነው አስፈላጊው ድጋፍ እየተረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኤርትራ ስደተኞች በአራት የስደተኛ መጠለያዎች ያገኙት የነበረው አገልግሎት ወደ ሁለት ዝቅ በማለቱ በሁለቱ መጠለያዎች የሚሰጠውን አገልግሎት አቅም ለመጨመር የሚያስችሉ አማራጭ የመፍትሔ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጓዳኝም ከሽመልባና ህጻጽ የወጡ ስደተኞችን አገልግሎት በሚሰጡ መጠለያ ጣቢያዎች የመመለስ ስራው እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ከ27 ሃገራት የመጡ ከ970 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞች አብዛኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.