Fana: At a Speed of Life!

የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የኮሮና ታማሚዎች የፅኑ ህሙማን ክፍል መሙላቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮቪድ19 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች መጨመርን ተከትሎ የፅኑ ህሙማን ክፍሉ ሙሉ በሙሉ መሙላቱ ተገለፀ፡፡
የፅኑ ህሙማን ክፍል በመሙላቱ ተጨማሪ ፅኑ ህሙማንን ሆስፒታሉ የመቀበል አቅም እንደሌለው የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት የህሙማን ቁጥር ቀንሶ እንደነበር እና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት ሰዎች በቀን ከሁለት የማይበልጡ እንደነበር ስራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በየቀኑ 25 የኮቪድ ህሙማን ወደ ሆስፒታሉ እየገቡ በመሆኑ የቁጥሮቹ ማሻቀብ የሶስተኛው ማእበል መግባቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ አሁን ላይ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው 100 ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን÷ ከእነዚህ ውስጥ 25 በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
በአጠቃላይ ሆስፒታሉ 400 የሚደርሱ ህሙማንን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 25 ፅኑ ህሙማንን ብቻ ማስተናገድ እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በፀና የታመሙትን ማስተናገድ የሚችለው ክፍሎቹ ሲለቀቁ ብቻ መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደጤና ሚኒስቴር መረጃ ከዘጠኝ ቀን በፊት በቫይረሱ ሲያዙ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 100 የማይሞላ ሲሆን፥ በዚህ ሳምንት በሚወጡ የምርመራ ውጤቶች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 500 የሚጠጋ ሆኗል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከ ትናንት እለት ብቻ ከ280 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
በዙፋን ካሳሁን
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.