Fana: At a Speed of Life!

የእነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ዋስትና ውድቅ ተደርጎ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ።

ወደ ቃሊቲ ማረሚያቤት እንዲወርዱ የታዘዘው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረሽብርና ህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ዐቃቤ ህግ ክስ ከመሰረተባቸው 21 ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ውስጥ ሰባቱ በትናንትናው እለት ችሎት ተገኝተው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን ከሳሽ ዐቃቤ ህግም የተፈጸፀመው ወንጀል የሰው ህይወት ያለፈበትመሆኑን በመጥቀስ ዋስትና ሊሰጥ አይገባም ሲል ተከራክሮ ነበር።

ፍርድ ቤቱ የዋስትና ክርክሩን መርምሮ በዛሬው ችሎት ውድቅ በማድረግ ወደ ቃሊቲ ማረሚያቤት እንዲወርዱ አዟል።

በቀጣይም ለመጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎት ያልተገኙ ተከሳሾች በተገኙበት ክሱን ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በተከሳሾቹ ላይ የተመሰረተው በአንደኛ ክስ ላይ ከ1ኛ አስከ 19ኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ የተመለከተ ነው፡፡

ተከሳሾቹ የሰሜን እዝ ጦር ሬዲዮ መገናኛን ለህወሓት ቡድን በመስጠት የሬዲዮ ኦፕሬሽን ባለሙያዎች እና የጥበቃ ባለሙያዎችን በማገትና በማስወገድ፣ የራሳቸውን የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን በማደራጀት በመተካት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰአት ከ30 ገደማ የሬዲዮ ግንኙነቱን በማቋረጥ እና በአካባቢው የመብራት አገልግሎትን በማቋረጥ የሰሜን እዝ ጦር ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ የሚለው ተጠቅሷል።
በ2ኛ እና በ3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ እና በ21ኛ ተከሳሾች ላይ የጦር መሳሪያ አስተዳደር አዋጅን በመተላለፍ ወንጀልን የሚመለከት ነው።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.